በኢትዮ ሱዳን አዋሳኞች የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮ ሱዳን አዋሳኞች የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
ኢዜአ ሀምሌ 23/2011በኢትዮጵያና በሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ በሱዳን ገዳሪፍ የኢትዮጵያ ቆንፅላ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በሱዳን የቡርሻ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልቃሲም ኢብራሂም በበኩላቸው "የሁለቱ ሀገራት መልካም ግንኙነት ለማሳደግና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማጠናከር ኃላፊነት ወስደን እሰራለን "ብለዋል ። የቆንፅላ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አምባሳደር አለማየሁ ወንድምአገኝ ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያና ሱዳን በምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ልማቶች የሚያደርጉትን ትብብር ዘላቂ ለማድረግ የሁለቱን ሀገራት ድንበር አካባቢ ፀጥታ ማስከበር ቅድሚያ ተሰጥቶ የሚሰራ ነው፡፡ በድንበር አካባቢ ያለውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅም ከማዕከላዊ መንግስታት የበለጠ ሚና መጫወት ያለባቸው የአጎራባች አስተዳደሮች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡ "በተለይም ከምዕራብ ጎንደር ዞን ጋር የሚዋሰኑ አራቱ የገዳሪፍ ግዛት ዲንደር፣ ምስራቅ ገለባት፣ ቡርሻና ባሶንዳ ዞኖች በቀጠናዊ የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ውይይት በማድረግ የጋራ ልማትን ማረጋገጥ አለባቸው "ብለዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የሕዝብ ለህዝብ ትስስር ጉዳይ በአዋሳኝ ባሉ አመራር ግንኙነት የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተልዕኳቸው ከዞንና ወረዳ ግንኙነት አልፎ ሀገራዊ አንድምታ እንዳለው አምባሳደር አለማየሁ አስረድተዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እያደገ የመጣና አሁን ካለበት ደረጃ የደረሰ ነው ያሉት አምባሳደሩ በልማቱ ዘርፍ ከሚያደርጉት ትብብር ጎን ለጎን አንዳንድ ችግሮች ሲከሰቱም ከማንም በፊት ቀድመው ከጎን መሰለፍ መጀመራቸው ሀገራቱ ምን ያክል የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህገ-ወጥነትን መከላከል፣ የጋራ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በባህልና በንግድ ማስተሳሰር፣ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡ የመኸር እርሻ መጀመሩን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት አርሶ አደሮች መካከል አለመግባባቶች በየጊዜው ቢከሰትም የሁለቱን ሀገራት መልካም ግንኙነት በጠበቀ መልኩ እየተፈቱ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሱዳን የቡርሻ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልቃሲም ኢብራሂም በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት መልካም ግንኙነት ለማሳደግና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማጠናከር አስተዳደራቸው ኃላፊነት ወስዶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ በዞኖች መካከል በሚኖሩ የልማት ስራዎች የአስተዳደር ሰራተኞችና የህዝቡ ተወካዮች እንዲገኙ በማድረግ እንዲሁም ህገ-ወጥነት፣ አላስፈላጊ የእርሻ ቦታ ማስፋት ዝንባሌንና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል አብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ዞኑን በሚያዋስኑ የዲንደርና ቡርሻ ዞን አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ባለፉት ወራት ወደ ሱዳን ተነድተው የነበሩ 98 የቀንድ ከብቶች ለኢትዮጵያውያን ባለንብረቶች ተመላሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ ”የምዕራብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮችና በሱዳን በኩል የአራቱ ዞን አርሶ አደሮች በጉርብትና የሚኖሩ በመሆናቸው እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉበትን መንገድ በአስተዳደር ኃላፊዎች በኩል የማመቻቸት ስራ ይሰራል” ብለዋል፡፡ የሱዳን 26 የልኡካን ቡድን አባላት ትናንት በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም መሳተፋቸውን ትናንት መዘገቡ ይታወሳል፡፡