ቀጥታ፡

ኮይካ ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚያደርግባቸውን መስኮች ለማሳደግ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ23/2019 የኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደርግባቸዋለሁ ያላቸውን አራት አዳዲስ መስኮች መለየቱን ይፋ አደረገ። የኢትዮ-ኮሪያ አልሙናይ ማህበር የምስረታ ጠቅላላ ጉባዔ ባለፈው ሳምንት ተካሂዷል። ኢዜአ በጉባዔው የተሳተፉትን የኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ የኢትዮጵያ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ሚስ ኪም ሱ ጂንን አነጋግሯቸዋል። ሚስ ኪም ሱ ጂን እንዳሉት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ የደቡብ ኮሪያ የልማት አጋሮች ዋነኛዋ ስትሆን ኤጀንሲውም እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከ1995 ጀምሮ ነው በኢትዮጵያ ስራ የጀመረው። በኢትዮጵያ የሚገኘው የኤጀንሲው ቢሮ በአፍሪካ ካሉት ትልቁ መሆኑን፤ በትምህርት፣ በጤና፣ በገጠር ልማት፣ በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በፈጠራ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በንጽህና አጠባበቅ የልማት መርሃ ግብሮች የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። ኮይካ በልማት ድጋፍ መርሃ ግብሩ አማካኝነት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ በጥራትና በብዛት የማሳደግ ዕቅድ እንዳለውና ለዚህም አራት አዳዲስ ዘርፎችን መለየቱን አስታውቀዋል። የእናቶችና ህጻናትን ሞት መቀነስ፣ የአምራች ዘርፉን የእሴት ሰንሰለት ማዘመን፣ የኢኮኖሚ ልማቱን ማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ስራዎች እንዲሁም የተፈናቃዮች፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች የተለዩ መስኮች ናቸው። ኤጀንሲው በተለይም የተፈናቃዮች፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾችን ችግር ለመፍታት ከሠላም ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመስራትና ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ምክትል ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። በእነዚህ መስኮች የሚደረገው ድጋፍ የሚጀመረው እ.አ.አ ከ2021 ጀምሮ ሲሆን በኤጀንሲው አሰራር መሰረት ድጋፍ ማድረግ ከሚጀመርበት ከሁለት ዓመት በፊት የስትራቴጂክ ሰነድ እንደሚዘጋጅ ሚስ ኪም ሱ ጂን አብራርተዋል። የስትራቴጂክ ሰነዱ በኤጀንሲው እየተዘጋጀ ሲሆን ሰነዱ ድጋፍ የሚደረግባቸውን መስኮች መሰረት በማድረግ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን እንደሚያካትትም ገልጸዋል። የሚተገበሩትን ፕሮጀክቶችና ስትራቴጂክ ሰነድ አስመልክቶ ከመንግስት ጋር ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል። ኮይካ በኢትዮጵያ በመጠጥ ውሃ፣ በንጽህና፤ በመስኖ እና በሌሎች ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ኤጀንሲው ከመደበኛ መርሐ ግብሩ በተጨማሪም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በሚከናወነው የ2ኛው ዙር የተጠናከረ ዋሽ አካውንት መርሐ ግብር 10 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ባለፈው መጋቢት ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል። ከተመደበው ገንዘብ ውስጥ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት፤ ቀሪው ሶስት ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ኮይካ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን እያከናወነባቸው ላሉ አካባቢዎች የገጠር ንጽህና ሽፋንን ለማሳደግ የሚውል ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም