በክልሉ ችግኞች በአግባቡ እንዲጸደቁ ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ችግኞች በአግባቡ እንዲጸደቁ ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው
ባህር ዳር (ኢዜአ) ሐምሌ 22 ቀን 2011-በአማራ ክልል ችግኞችን ተክሎ ከመሄድ ባለፈ በአግባቡ እንዲጸድቁ ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። እንደ ሀገር ዛሬ ለመትከል ከታቀደው 200 ሚሊዮን ችግኝ100 ሚሊዮን የሚሆኑት በአማራ ክልል በመተከል ላይ መሆኑ ተመልክቷል። ዛሬ በዘንዘልማ በተባለ አካባቢ በተካሄደ የችግኝ ተከላ ቢሮውን ወክለው የተገኙት በክልሉ ግብር ቢሮ የአግሮ ፎረስተሪ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ወንድምኩን እንደገለጹት እንደሀገር በተያዘው ዓመት ሊተከል ከታቀደው 4 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የሚሆነው በአማራ ክልል ውስጥ የሚተከል ነው፡፡ እስከ ትናንት ባለው ጊዜ ከ800 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል። “ዛሬ በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ከ700 በላይ የችግኝ መትከያ ቦታዎች ተለይተው ተከላ እየተካሄደ ነው” ሲሉም ገልጸዋል። አቶ ሰለሞን አንዳሉት በችግኝ ተከላ መርሀግበሩ ላይ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ የሴቶችና ወጣት አደረጃጀትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። እስከዛሬ ሲተከሉ ከነበሩ ችግኞች ይጸድቁ የነበሩት 65 በመቶ ብቻ እንደነበር ያስረዱት አቶ ሰለሞን ዘንድሮ 80 ከመቶ በላይ የመጽደቅ ምጣኔ እንዲኖር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ዘንድሮ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ያለምንም ችግር ጸድቀው ማደግ እንዲችሉ ጥበቃና ክብካቤ የሚያደርግ እንደሚቀጠር ያስረዱት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተወካይ አምባሳደር ውለታው ኃይለማሪያም ናቸው። “ዋናው ነገር ችግኝ መተከል ሳይሆን እንዲጸድቅ ማድረግ ነው” ያሉት አምባሳደር ውለታው ለእዚህም መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እስፈላጊውን ስራ እንደሚያከናውን አመልክተዋል ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የመጽደቅና የማደግ መጠናቸውን መከታተልና መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉአለም ናቸው። “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤቴክርስቲያን ዛሬም በሀገር አቀፍ ደረጃ ላለው ውስን የደን ሀብት ባለውለታ ናት” ያሉት መላከ ሰላም ኤፍሬም በቀጣይም ዛፍ በመትከልና ደንን በመንከባከብ በኩል የድርሻዋን እንደምትወጣ አመልክተዋል። መንግስት ችግኞች በዘመቻ እንዲተከሉ ከማድረግ ባለፈ በአግባቡ እንዲጸድቁ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል። “በእስልምና እምነት ችግኞችን መንከባከብ ሃይማኖታዊ ግዴታ ጭምር ነው “ ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል አስልምና ጉዳዮች የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሸህ ዘይን ያሲን ናቸው። ዛፎች የአየር ጸባይ እንዳይዛባ ፋይዳቸው የጎላ በመሆኑ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የተተከሉ ችግኞችን ከዘመቻ ስራ ባለፈ ሃይማኖታዊ ትርጉም ሰጥቶ እንዲንከባከብ መክረዋል። "ችግኝ ለመትከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንዳደረገ ሁሉ ጸድቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የጋራ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል" ያለቸው ደግሞ ኮንስታብል ጊዜወርቅ መከተ ናት። እንደእርሷ ገለጻ በተከላ ሥራው የተሳተፉ የተለያዩ አካላት በተለያዩ ጊዜያት ችግኞቹን ሊንከባከቡና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል። በአማራ ክልል በዛሬው እለት በተከናወነው የችግኝ ተከላ ሥራ እስከ ቀኑ 9:00 ሰዓት ብቻ ከ58 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል መቻሉ ታውቋል፡፡