ቀጥታ፡

የትግራይ ክልል ሦስት ክለቦች ወደ የተባበሩት ዓረብ ኢሜሬትስ ያቀናሉ

መቐለ ሓምሌ 22 / 2011 የትግራይ ክልል ሦስት ክለቦች በተባበሩት ዓረብ ኢሜሬትስ በሚካሄዱ የቅድመ ውድድር የወዳጅነት ጨዋታዎች ሊያደርጉ ነው። የአልነጃሺ ኢትዮጵያ ቱር ኤንድ ትራቭል ፕሬዚዳንት መምህር ያሲን ራጁ እንዳሉት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮኑ መቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ወልዋሎ ዓዲግራትና ስሑል ሸሬ በዱባይ በሚከናወኑ ጨዋታዎች ይሳተፋሉ። ክለቦቹ  ግጥሚያቸወን የሚያደርጉት ከነሐሴ 20-30/2011 ባለው ጊዜ ሲሆን፣ግጥሚያዎቹ የሚያካሂዱት ከሶስት የአገሪቱ ክለቦች ጋር እንደሚሆን ተናግረዋል። ጨዋታዎቹ የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት፤ወጣቶች በስፖርት ታንፀው ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራትና ልምድ ለመቅሰም ዓላማ እንዳላቸው አብራርተዋል። ጨዋታዎቹ እግር ኳስ ለፍቅር ለወዳጅትና ለጤንነት በሚል መርህ  የሁለቱ አገሮችን  የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር እንደሚደረጉ መምህር ያሲን  አስረድተዋል። ክለቦቹ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የትብብር ደብዳቤ እንደተጻፈላቸው አስታውቀዋል። የወልዋሎ ዓዲግራት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ አማረ በሰጡት አስተያየት ክለባቸው  ከአገሪቱ ክለቦች ጋርም በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ወዳጅነትን ለመፍጠርና ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጥር ገልጸዋል። የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሸን ጽህፈት ቤትኃላፊ አቶ አንገሶም ካሕሳይ ክለቦቹ አጋጣሚውን ዓለም አቀፍ ልምድ ለማግኘት፣ከባለሃብቶች  ጋር ለመተዋወቅና የስፖርት አካዳሚ ለመክፈት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አስታውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም