ቀጥታ፡

ችግኞች መትከልና ተንከባክቦ ማዕደቅን ልምዳቸው እንደሚያደርጉ የሐረሪ ክልል ነዋሪዎችና የሠራዊት አባላት ገለጹ

ሐረር ሐምሌ 22 / 2011 ችግኞች መትከልና በዘለቄታነት ተንከባክቦ የማዕደቅ ሥራን ልምዳቸው እንደሚያደርጉ የሐረሪ ክልል ነዋሪዎችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተናገሩ። ነዋሪዎቹና አባላቱ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ዛሬ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል። በተከላው የተሳተፉት ወይዘሮ ዝናሽ ተፈራ በክልሉ ሸንተረር፣ ተፋሰስ፣አረንጓዴ ስፍራዎች በሌሎች ቦታዎች ላይ ችግኞችን የመትከልና የማጽደቅ ስራን ባህልና ልምድ አድርገዋለሁ  ብለዋል።በመኖሪያ  ግቢያቸው ያካበቱትን ልምድ በማስፋት። አያቶቻችን ያስረከቡንን አረንጓዴ ልምላሜ በአግባቡ ሳንይዘውና ለትውልድ መልሰን ተክለን ባለማጽደቃችን  አካባቢያችንን በራሳችን ጥፋት አራቁተነዋል ያሉት ወይዘሮ ሰሚራ ሐጂ ዩሱፍ  የተባሉ አስተያየት ሰጪ፣አሁን ተራው ችግኝ የመትከልና የማጽደቅ ሆኗል ይላሉ። አገርንና አካባቢን በአረንጓዴ እጽዋት ማሳመር ንጹህ አየር እንድትነፍስ በማድረግ  ውስጥህ በደስታ እንዲሞላ ስለሚያደርግ ሁሌም ችግኝ መትከልን ባህሌ አደርገዋለሁ ያለው ደግሞ ወጣት በሐር አሊ ነው። በተለምዶ ቀላዳንባ በሚባለው አካባቢ ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ችግኞች የተከሉት የ13ኛ በላይ ዘለቀ ክፍለ ጦር  ስታፍ መምሪያ ሠራዊት አባላት የተለያዩ ዝርያ ያላቸውና ለአካባቢው ተስማሚነት ያላቸው ችግኞች ተክለዋል። የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አሊጋዝ ገብሬ ''ሠራዊቱ በረሃማነትንና የአፈር መሸርሸርን በአረንጓዴ ልማቱ ላይ በመሳተፍ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ መወጣት አለበት”ብለዋል። አባላትም ወታደራዊ ግዳጁ በድል እንደሚፈጽመው ሁሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ አንደሚሰሩ ገልጸዋል። በሐረሪ ክልል በአረንጓዴ አሻራ ቀን 190ሺ ችግኞች በዛሬው እለት ተተክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም