ቀጥታ፡

የብሔራዊ ባንክ ሰራተኞች ከአራት ሺህ በላይ ችግኞች ተከሉ

ሀምሌ 22/2011 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማኔጅመንትና ሰራተኞች አቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው የባንኩ ማሰልጠኛ ማዕከልና በዋናው መስሪያ ቤት አራት ሺህ 700 ችግኞች ተከሉ። የአካባቢን የአየር ሁኔታ ነፋሻማ ከሚያደርጉ በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችም ተተክለዋል። በ'አረንጓዴ አሻራ' ቀን የተተከሉ ችግኞች እስከሚጸድቁ ድረስ እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ሰራተኞቹ ገልጸዋል። በችግኝ ተከላው ወቅት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን ተቋማት ምክትል ገዢ አቶ ጥሩነህ ሚጠፋ እንዳሉት፤ ባንኩ መርሃ-ግብር በመቅረጽ ችግኞቹ እስኪጸድቁ ድረስ እንክብካቤ ያደርጋል። ከዚህ በፊት የነበረው ልምድ ችግኞችን የመትከል እንጂ የመንከባከብ አይደለም ያሉት አቶ ጥሩነህ ዘንድሮ የሚተከሉት አራት ቢሊዮን ችግኞች እንዲጸድቁ ሁሉም እንክብካቤ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ የማነ ዮሴፍ በበኩላቸው ዜጎች ችግኝ በመትከል አሻራ አስቀምጠናል ማለት የሚችሉት የተተከሉትን በመንከባከብ እንዲጸድቁ በማድረግ ሲችሉ ነው ብለዋል። ችግኞች በተተከሉባቸው አካባቢዎች ካለው ኅብረተሰብ ጋር በመተባበር ችግኞቹ እንዲጸድቁ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የለውጥ ማንጅመንት ዕቅድና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አባተ ምትኩ እንዳሉት፤ ችግኞችን ከመትከል ሳይሆን ጸድቀው የሚፈለገውን ጥቅም እንዲሰጡ እንክብካቤ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ከባንኩ ሰራተኞች መካከል አቶ መዝሙር ብርሃኑ የችግኝ ተከላው አገራዊ አንድነት የሚያጠናክር በመሆኑ በየዓመቱ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል። በተለይም በመጪው በጋ የተተከሉት ችግኞች እንዳይደርቁ በየጊዜው ውሃ በማጠጣት እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። የባንኩ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዋና መኮንን ወይዘሮ አምባወርቅ መኮንን ደግሞ ዛሬ በማሰልጠኛ ማዕከሉ የተተከሉት ችግኞች እንዲጸድቁ በባለሙያዎች የቅርብ ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል። በአቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማሰልጠኛ ማዕከል በተካሄደው የችግኝ ተከላ ከ800 በላይ ሰራተኞች ተሳትፈዋል። ባንኩ በአዲስ አበባ ባሉ የመንገድ አካፋዮች ላይ ዕፅዋት በመትከልና በማስዋብ በኩልም ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም