የወላይታ ህዝብ ታላቋን ኢትዮጵያ እንዲገነባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
የወላይታ ህዝብ ታላቋን ኢትዮጵያ እንዲገነባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 22/2011የወላይታ ህዝብ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የከፈለውን መስዋእትነት አሁንም ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ለተጀመረው ጥረት ሊጠቀምበት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አሳሰቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከወላይታ ሶዶ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ጀምረዋል። የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ በከተማው ስታዲየም ተገኝቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደማቅ አቀባበል አድርጓል። በዚሁ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የወላይታ ህዝብ የአገሩን ዳር ድንበር በማስጠበቅ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው ብለዋል። ''ዛሬ እኔ እዚህ የተገኘሁት ሰኔ 16 ቀን በአዲስ አበባ በተሞከረው ጥቃት እኔን ለማዳን ሲል ራሱን በሰዋው ዮሴፍ አያሌው ስም ነው'' በማለት ገልፀዋል። የወላይታ ህዝብ ከአደዋ ጀምሮ እስከ ስኔ 16ቱ ጥቃት ለኢትዮጵያ አንድነት ግንባሩን የሰጠ ህዝብ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የወላይታ ህዝብ የመደማመጥና የመወያየት ባህልን ጨምሮ በግጭት አፈታት፣ በዳኝነትና በሽምግልና ያለውን እሴት ዛሬም ድረስ ጠብቆ በማቆየት ግንባር ቀደም መሆኑንም አውስተዋል። በመሆኑም ህዝቡ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የከፈለውን መስዋእትነት አሁንም ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ሊጠቀምበት እንደሚገባ አሳስበዋል። የወላይታ ህዝብ ነዋሪዎችም የፈረስ፣ ጋሻና ጦር ስጦታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማበርከት ያላቸውን ክብር ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ከህዝቡ ጋር ያደረጉትን ቆይታ አጠናቀው በወላይታ ጉተራ አዳራሽ ከተለያዩ የዞኑ ህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ውይይት ጀምረዋል። በውይይቱ ላይም ነዋሪዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል። ከጥያቄዎቹ መካከልም የወላይታ በክልልነት መደራጀት፣ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር፤ የኢንዱስትሪ ፓርክና የአየር ማረፊያ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ይገኙበታል። ከውይይቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ይስጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ዛሬ ጠዋት ከወላይታ ህዝብ ጋር በመሆን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ችግኝ ተክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።