ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ አሻራ ቀን ያሳዩትን ተነሳሽነትና አንድነት በሌሎችም አገራዊ ስራዎች እንዲቀጥል ተጠየቀ

ሀምሌ 22/2011 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ አሻራ ቀን ያሳዩትን አንድነትና ተነሳሽነት በሌሎችም አገራዊ ስራዎችም እንዲቀጥሉ በችግኝ መትከል መርሃ ግብር የተሳተፉ የግል ባንኮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። ዛሬ በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል የአረንጓዴ አሻራ ቀን በጀሞ ቁጥር 1፣ 2፣ 3 እና በተለምዶው ኃይሌ ጋርመንት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 16 የግል ባንኮች፣ የኢትዮ-ቴሌኮምና ሌሎች የግል ድርጅቶች ሰራተኞችና የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በእነዚህ አካባቢዎች ተገኝቶ እንደተመለከተው የባንክ ሰራተኞችን ጨምሮ ህጻናት፣ አዛውንቶች፣ እናቶችና በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ ችግኝ ተክለዋል። በመርሃ ግብሩ የተገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዝናብ፣ ብርድና ሌሎች መሰናክሎችን ተቋቁመው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምረው ችግኝ ለመትከል ያሳዩት ተነሳሽነትና ፍላጎት የተለየ እንደነበርም በቦታው በነበርንበት ወቅት መታዘብ ችለናል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የግል ባንኮች፣ የኢትዮ-ቴሌኮም ሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኝ መትከል በሚለው መርሃ ግብር ላይ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን ልዩ ስሜት ገልጸዋል። ወይዘሮ ሄዋን ጌታቸው-ከህብረት ባንክ እንዲሁም አቶ ኤፍሬም ላቀው-ከኢትዮ-ቴሌኮም መርሃ ግብሩ በቋሚነት የምንሰራው እንጂ  የዘመቻ ስራ መሆን የለበትም ያሉት ተሳታፊዎቹ ለአገራዊ ምጣኔ ሃብት እድገት፣ ለፖለቲካዊ መግባባትና ሌሎች አገራዊ አንድነትን ለማምጣትም በእለት ተእለት ተግባራችን ልንከውነው ይገባል ሲሉም ጨምረዋል። ኢትዮጵያ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች አገር እንደመሆኗ ችግኝ ለመትከል ያሳዩትን አንድነት በሌሎች ስራዎችም ማሳየት እንዳለባቸው በአጽንኦት ተናግረዋል። አቶ አበባው ዘውዴ-ከቡና ባንክ፤ ወይዘሮ የድል ፍሬ አበበ-ከብርሃን ባንክ፣ አቶ ረሺድ አብዱልከሪም-የአካባቢው ነዋሪ የባንኮቹ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች "ባንክ ያለ ገንዘብ መንቀሳቀስ እንደማይችል ሁሉ የሰው ልጅም ያለ ዛፍ ሙቀትን ተቋቁሞ መቀጠል ይከብደዋል" በማለት የችግኝ መትከል ጠቀሜታን ገልጸዋል። አቶ መቻል በዳዳ-ከዘመን ባንክ፣ ወጣት አብዱል ሰላም መሃመድ የአካባቢው ነዋሪ በአካባቢው ለችግኝ ተከላው የወጣው የባንኮቹ ሰራተኞችና የአካባቢው ማህበረሰብን ቁጥር ያማከለ ችግኝ ባለመቅረቡ ህዝቡ ሲጉላላ ተመልክተናል። በተጨማሪም የተቆፈሩ ጉድጓዶችም ከተሳታፊው ቁጥር ባለመገናዘቡ የመትከያ ጉድጓዶች እጥረትም ተስተውሏል። በዛሬው የአረንጓዴ አሻራ ቀን መላው ኢትዮጵያውያን በተደረገላቸው አገራዊ ጥሪ መሰረት በመላው የአገሪቷ አካባቢዎች በንቃት ሲሳተፉ ተስተውለዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ዛሬ ግማሽ ቀን ከመሆኑ በፊት በዓለም የተያዘው የአንድ ቀን ችግኝ ተከላን ሪከርድ ለመስበር ችላለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም