ቀጥታ፡

የተተከሉት ችግኞች ፀድቀው ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ የእንክብካቤ ስራ ለመስራት የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ይሰጣል

አዲስ አበባ ኢዜአ ሐምሌ 22/2011 አራት የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የተከሉትን ችግኞች ለመንከባከብ እንዲችሉ ቦታው በጂ.ፒ.ኤስ/አቅጣጫ ጠቋሚ /መሳሪያ እንዲካተት ለማድረግ ማቀዳቸውን ገለጹ። ዛሬ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሔደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በገላን ልዩ ስሙ  ቢልቢሎ በሚባል አካባቢ ከአራት በላይ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ተገኝተዋል። በዋናነትም ከነዚሁ ሰራተኞት ውስጥ የግብርና ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴርና የፕላንና ልማት ኮሚሽን እንዲሁም የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሰራተኞች ይገኙበታል። በተከላውም ከሰባት ሺህ በላይ ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በሰው እስከ 40 የሚደርስ ችግኝ እንደተተከለ ነው አስተባባሪዎች የገለጹት። ሰራተኞቹ እንደሚሉትም እነዚሁን ችግኞት ለመንከባከብና ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ ለማድረግም በጂ.ፒ.ኤስ ወይም በአቅጣጫ ጠቋሚ መሰሪያዎች ውስጥ አንዲካተት ተደርጎ የመንከባከብ ስራውን ለመራት ማቀዳቸውን ነው የሚገልጹት። አስተያየታቸውን ከሰጡት ችግኝ ተካዮች ውስጥ አቶ ዘላለም ብርሃኔ እንደሚሉት ዛሬ በርካታ ኃይል መጥቶ የችግኝ ተከላውን ማካሔዱ አንድ እርምጃ ነው። ነገር ግን ችግኞቹ ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ መስሪያ ቤታቸውና ሌሎች ተቋማት በመሆን ቦታው በአቅጣጫ ጠቋሚ መሳሪያ ወይም ጂ.ፒ.ኤስ ውስጥ እንዲካተት አድርገናል ነው ያሉት። ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ እስክንድር ተስፋዬ ደግሞ የችግኝ ተከላው መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ከሆነበት እለት አንስቶ በጉጉት ስንጠብቅ ነበር ብለዋል። በመሆኑም ዛሬ በርካታ ዳገትና ቁልቁለትን ወጥተን የተከልነው ችግኝ ፀድቆ አገራችንን ከበረሃማነት ለመታደግና የአረንጓዴ አሻራችንን ውጤታማ ለማድረግ መስራት ይገባናል ነው የሚሉት። ይሕ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአገሪቷ መላው ሕዝብ በአንድነት ለጋራ እቅድ እንዲቆሙ ያደረገ በመሆኑም ለውጤታማነቱም እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን መወጣት አለበት ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ኤልሳቤት ባልቻ ናቸው። በአንድ ቀን ዘመቻው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዜናው እስከተጠናከረበት ጊዜ ብቻ ከ232 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም