''የአፋር ክልል ሕዝብ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠው ትኩረት መጠናከር አለበት''-የብሄራዊ ባንክ ገዢ - ኢዜአ አማርኛ
''የአፋር ክልል ሕዝብ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠው ትኩረት መጠናከር አለበት''-የብሄራዊ ባንክ ገዢ
ሰመራ ሐምሌ 22 ቀን 2011 የአፋር ክልል ሕዝብ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠው ትኩረት መጠናከር እንዳለበት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢዶክተር ይናገር ደሴ ተናገሩ። ገዢው በአፋር ክልል ገቢረሱ ዞን ዱለሳ ወረዳ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከተሳተፉ በኋላ እንዳስታወቁት ሕዝቡ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያደርገው ጥረት መጎልበት አለበት። በተከላው ላይ ያዩት ሕዝቡ ለአረንጓዴ ልማት ላይ ያለውን አቋምና ጥንካሬ ያሳያል ያሉት ዶክተር ይናገር፣ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ ተመልክቼያለሁ ብለዋል። ተከላው አንደ አፋር ክልል ባሉ ከፍተኛ ሙቀትና የዝናብ እጥረት በሚታይባቸው መከናወኑ ድርቅን ለመከላከል እንደሚያስችልም ገዢው አስታውቀዋል። ''ተከላው የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን፤ የህልውና ጉዳይ ነው'' ብለዋል። ኅብረተሰቡ በተከላው ላይ ያሳየውን ተሳትፎ በማጽደቁም መድገም እንደሚጠበቅበት ዶክተር ይናገር አሳስበዋል። የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ሁሴን በኩላቸው በገቢ-ረሱ ዞን ከ77 ሺህ በላይ ችግኞች እየተተከሉ መሆናቸውንና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከታቀደው በላይ እንደሚከናወን እምነታቸውን ገልጸዋል። ክልሉ ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግኝ ከመትከል በተጓዳኝ ለማጽደቅ ትኩረት መሰጠቱንና በዚህም የመንግሥት ተቋማት የመንከባከብና የማጸደቅ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ተናግረዋል። የአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ነዋሪው ወጣት ኡመር ኢብራሂም ተከላው በክልሉ በከሰል ሥራ የተመናመነውን የደን ሽፋን እንዲያገግም ይረዳል ብለዋል። በተጨማሪም የአካባቢውን የአየር ንብረት በመለወጥ ለሰውም ሆነ በአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ ለሚገኙ የዱር እንስሳት የተሻለ መኖሪያ እንደሚያደርገው እምነቱን ገልጿል።