ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለ2022 የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ከሌሴቶ ጋር ትጫወታለች

አዲስ አበባ ኢዜአ ሐምሌ 22/2011 ኳታር እንደ አውሮጳዊያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2022 ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያ ከሌሴቶ ጋር ትጫወታለች። ዛሬ በግብጽ ካይሮ በወጣው ዕጣ በእግር ኳስ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሚባሉ 28 የአፍሪካ አገራት ቡድኖች በቅድመ ማጣሪያው ተካተዋል። ኢትዮዮጵያም ዝቅትኛ የእግር ኳስ ደረጃ ካለቸው አገራት ተርታ በመመደቧ  በቅድመ ማጣሪያው ተደልድላለች። የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆነችው ሌሴቶ ባለፈው ወር በወጣው ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ 144ኛ ስትሆን ኢትዮጵያ 150ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ዛሬ በወጣው የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ዕጣ ኤርትራ ከናሚቢያ፣ ሶማሊያ ከዚምባቢዌ፣ ቡሩንዲ ከታንዛኒያ፣ ቦትስዋና ከማሊ፣ ጋምቢያ ከአንጎላ፣ ሞሪሺየስ ከሞዛምቢክ ይጫወታሉ። ቡድኖቹ የሚያደርጉት የመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ እ.አ.አ ከመስከረም 2-10 ቀን 2019 ባሉት ቀናት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል። በቅድመ ማጣሪያው በደርሶ መልስ አሸናፊ የሚሆኑ 14  ብሄራዊ ቡድኖች በቀጣዩ ዙር በእግር ኳስ ደረጃቸው የተሻሉ ከሚባሉት 26 ቡድኖች ጋር  በምድብ ተደልድለው የመጨረሻውን የማጣሪያ ውደድር ያደርጋሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም