ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን የበለፀገች የማድረግ ብቃቱ እንዳላቸውም ችግኝ በመትከል አሳይተዋል - አምባሳደር መለስ ዓለም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን የበለፀገች የማድረግ ብቃቱ እንዳላቸውም ችግኝ በመትከል አሳይተዋል - አምባሳደር መለስ ዓለም
አዲስ አበባ ኢዜአ ሐምሌ 22/2011 ''ኢትዮጵያን የበለፀገች ማድረግ የልጆቿ ኃላፊነት እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ይህን የማድረግ ብቃቱ እንዳላቸውም ችግኝ በመትከል አሳይተዋል'' ሲሉ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ። በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ ቀንን በማስመልከት የችግኝ መትከል ስነ-ስርዓት ተካሂዷል። በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ ኬንያውያን የአረንጓዴ አሻራ ቀንን በማስመልከት በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ችግኝ ተክለዋል። በችግኝ መትከል ስነ-ሰርዓት ላይ በኬንያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ አምባሳደር መለስ ዓለም ባደረጉት ንግግር ''ኢትዮጵያውያኑ በዚህ ተግባር ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ለመንግስት የሚያደርጉት ድጋፍ በቦታ ርቀት የማይወሰን መሆኑን አሳይተዋል'' ብለዋል። ''ኢትዮጵያውያን በክፉም ሆነ በበጎ በጋራ የመቆም ልምድ አላቸው ያሉት'' አምባሳደር መለስ በአገር ቤት ዛፍ በመትከል ያሳየውን ህብረትና አንድነት በሁሉም የአገር ግንባታ መስክ መድገም እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል። ''ኢትዮጵያን የበለፀገች ማድረግ የልጆቿ ኃላፊነት እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ይህን የማድረግ ብቃቱ እንዳላቸውም ችግኝ በመትከል አሳይተዋል'' ብለዋል። በዘንድሮ የክረምት ወቅት አራት ቢሊዮን የዛፍ ችግኝ ለመትከል የተያዘው የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር አንዱ አካል የሆነው 'አረንጓዴ አሻራ ቀን' ከዕቅዱ በላይ እውን መሆኑ ታውቋል። ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር መረጃ ቋት እየወጣ ባለው መረጃ መሰረት በዛሬው ዕለት ከ224 ሚሊዮን ችግኝ በላይ በመትከል ከዕቅዱ በላይ ማሳካት ተችሏል። ዛሬ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 'የዜጎች የአረንጓዴ አሻራ ቀን' በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን በመተከል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ ክብረወሰን ለማስመዝገብ አቅዳ ስትሰራ መቆየቷ ይታወቃል።