የኢንተርፕራይዙ ሰራተኞች በአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ችግኝ ተከሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንተርፕራይዙ ሰራተኞች በአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ችግኝ ተከሉ
አዳማ ኢዜአ ሐምሌ 22/2011 የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ሰራተኞች የአዲስ– አዳማ የፍጥነት መንገድን ውበት ለማላበስ ችግኝ ተከሉ። በችግኝ ተከላው ላይ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት ሰራተኞች መካከል ወጣት ማስታወሻ ቤለማ ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፏ ኩራት እንደተሰማት ተናግራለች። በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች በደን ሀብት ላይ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመተካት የሁሉንም አካላት ተሳትፎ ስለሚጠይቅ በችግኝ ተከላው ላይ መሳተፏን ገልጻለች። ወጣቷ እንዳለችው በተለይ በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ዳርቻ ላይ ችግኝ መተከሉ ለመንገዱ ውበት ከማላበስ ባለፈ አሽካርካሪዎች ንፁህ አየር እንዲተነፍሱ ያግዛል። ሌላው የአንተርፕራይዙ ሰራተኛ አቶ ገመቹ ተሰማ በበኩላቸው ከቢሾፍቱ አዳማ የፍጥነት መንገድ ዳርቻ ላይ የተከሉትን 22 ችግኞች በየወሩ እየተመላለሱ ለመንከባከብ ማቀዳቸውን ተናግረዋል። እሳቸውን ጨምሮ የኢንተርፕራይዝ ሰራተኞች በመንገዱ ዳርና ዳር ችግኝ መትከላቸው በከፍተኛ ወጪ ለተገነባው አስፓልት መንገድ ደህንነት መጠበቅ እንደሚረዳው ጠቁመዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ጥሪ ተከትለው በችግኝ ተከላው በመሳተፍ የራሳቸውን አሻራ ለማኖር መሳተፋቸውን የሚገልፁት ደግሞ ሌላው ሰራተኛ አቶ ደምስ አማረ ናቸው። ህዝቡም በመርሃ ግብሩ ለመሳተፍ ያሳየው መነሳሳት አስደሳች መሆኑን የሚናገሩት አቶ ደምስ "በየዓመቱ ችግኝ ተከላው ባህል ሆኖ መቀጠል አለበት "ብለዋል ።