ቀጥታ፡

በችግኝ ተከላው የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የተሰማሩ የፀጥታ አካላት ገለጹ

ኢዜአ ሀምሌ 22/2011 ሰላምን ከማስከበር ጎን ጎን ችግኝ በመትከል በሀገር ልማትና እድገት ላይ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን  በስራው የተሰማሩ የፀጥታ ኃይሎች ገለጹ ። በዞኑ አባይጮመን ወረዳ በችግኝ ተከላው እየተሳተፉ ካሉት የጸጥታ አካላት መካከል የፌዴራል ፖሊስ አባል ሳጂን አሰፋ አምሳሉ አንዱ ናቸው። ሳጅን አሰፋ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት የህዝቡን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን በአረንጓዴአሻራ ቀን ችግኝ በመትከል የድርሻቸው እየተወጡ  ነው ። ”ችግኝ መትከል ህይወት ማቆየት መሆኑን በመገንዘብ የፀጥታ አካላት በተከላው ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን በመፈፀም ላይ ናቸው” ብለዋል። የፀጥታ ሃይሉ ሰላም በማሰከበር ያሳየውን አኩሪ ተግባር በልማት መስኩ ለመድገም  እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል ። ሌላኛው የመከላከያ ሰራዊት አባል ኢንስፔክተር መቲክን  አሊ በበኩላቸው  "የጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድ ከማሳካት አኳያ ገንቢ ሚና በመጫወት ላይ ነን "ብለዋል። በዚሁም ፀጥታ ሃይሉ በዋናነት የህብተረቡ አገልጋይ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው የችግኝ ተከላው የዚሁ አንድ አካል መሆኑን አስረድተዋል ። የአባይ ጮመን ወረዳ  ዋና አሰተዳዳሪ  አቶ አብዱላሂ አመ "ችግኝ መትከል በአካባቢው ለሚገኙ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ጠቀሜታው  የጎላ ነው " ብለዋል ። በአካባቢው ያካሔዱት የችግኝ ተከላ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር የሚያንፀባርቅ መሆኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም