በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ዘመናዊ የአውቶብስ መናኸሪያ ግንባታ ተጀመረ

73
ጅማ ሰኔ 5/2010 በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ  ዘመናዊ የአውቶብስ መናኸሪያ ግንባታ መጀመሩን የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ፡፡ ከንቲባ  አንበሴ ኡርኮ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የደቡብ ክልል መንግስት በመደበው 15 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ የመናኸሪያ ግንባታ ስራ ከተጀመረ ሁለት ሳምንታትን አስቆጥሯል። በ15 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ የሚያርፈው የዚሁ መናኸሪያ ግንባታ ሶስት የቢሮ ህንጻ ፣ የተገልጋይ ማሪፊያ፣ ካፌ፣  የመረጃ  ማዕከል፣ ሚኒሚዲያና ለመንገደኞች አገልግሎት የሚሰጡ መጸዳጃ ቤቶችን ያካተተ ነው፡፡ የመናኸሪያው መገንባት የትራንስፖርት አገልግሎትን ከማሳለጥ ባለፈ የንግዱ እንቅስቃሴ በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያስገኝ  ከንቲባው ተናግረዋል። የመናኻሪያው ግንባታ በአሁኑ ወቅት ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ከታርጫ- አሰንዳቦና ጅማ እንዲሁም ከወላይታ-  ታርጫ እና ከታርጫ- ጭዳ የተጀመሩ አዳዲስ የአስፓልት መንገድ ስራ ሲጠናቀቅ በርካታ ተሽከርካሪዎችን በቀን ለማስተናገድ የመናኸሪያው ጠቀሜታ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል። የታርጫ ከተማ ነዋሪ አቶ ደስታ ዋኮ በሰጡት አስተያየት  ''የታርጫ ከተማ ከተመሰረተች ገና 16 አመቷ በመሆኑ የከተማው አስተዳደርና ነዋሪው ለልማት ስራዎች ተቀራርበው ሊሰሩ ይገባልም'' ብለዋል። በመናኸሪያው አካባቢ የምትገኝ ወጣት አስናቀች ታዬ በበኩሏ የመናኸሪያው መሰራት ለሷና ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር ያላትን እምነት ገልጻለች፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም