ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ የተከለውን ችግኝ በመንከባከብ የአረንጓዴ ልማት አሻራውን ማኖር አለበት--- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዳማ ኢዜአ ሃምሌ 22/2011-ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ የተከለውን ችግኝ በዘላቂነት በመንከባከብ በአረንጓዴ ልማት ላይ አሻራውን ማኖር እንዳለበት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስገነዘቡ። ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸውና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በቢሾፍቱ ከተማ አየር ሃይል አካባቢ በሚገኘው ተራራ ላይ በመገኘት ችግኝ ተክለዋል። በዚህ ወቅት አቶ ሽመልስ ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ የተከለውን ችግኝ በመንከባከብ በአረንጓዴ ልማት ላይ የራሱን አሻራ ማኖር እንደሚገባም አሳስበዋል ። የኦሮሚያ የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ከትግል ወጥቶ ወደ ልማቱ ፊቱን የመለሰበት ዕለት መሆኑን ተናግረዋል። የኦሮሞ ህዝብም ሆነ መላው የኢትዮጰያ ህዝብ ቀኑን በችግኝ ተከላ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ አረንጓዴ ልማት በንቃት መሳተፉን እንደሚቀጥል የሚያረጋግጥበትና ቃሉን የሚያድስበት አድርጎ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል ። "የችግኝ ተከላ የአንድ ዕለት ወይም የአንድ ጊዜ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ወደ ነበረችበት አረንጓዴነትና ልምላሜ እንድትመለስ በዘላቂነት ችግኞችን መትከልና የተከልናቸውን በእንክብካቤ ማሳደግ ይኖርብናል "ብለዋል። በችግኝ ተከላ ቦታው ላይ የተሳተፈው ህፃን ተስፋዬ ሀብታሙ በሰጠው አስተያየት "ችግኝ የምንተክለው አካባቢያችን ለምለም ለማድረግና ንፁህ አየር ለማግኘት ጭምር በመሆኑ በአቅሜ በተከላው ተሳትፌያለሁ "ብሏል ። በችግኝ ተከላው ላይ የከተማውን ህብረተሰብ ጨምሮ ከግልና ከመንግስት ባንኮች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የአየር ሃይል አባላትን ፣ የሃይማኖት መሪዎችንና በሺህዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም