ቀጥታ፡

የኢዜአ ሰራተኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከ500 መቶ በላይ አገር በቀል ችግኞችን ተከሉ

ሐምሌ 22 ቀን 2011 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከ500 በላይ አገር በቀል ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል። የተቋሙ ሰራተኞች ዛሬ የተከሏቸው ችግኞች አገር በቀልና ዝርያቸው እየተመናመኑ የሚገኙ መሆናቸውም ታውቋል። የዜና አገልግሎት ምክትል ዋና  ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ተቋሙ እንደ መገናኛ ብዙሃን ህበረተሰቡ ችግኝ እንዲተክል መቀስቀስና ማነሳሳት ብቻ ሳይሆን በችግኝ ተከላው መርሃ ግብርም ሰራተኞቹን ይዞ ተሳታፊ ለመሆን ያለመ መርሃ ግብር ፈጽሟል። ህብረተሰቡ በየጊዜው በሚያገኘው መረጃ ችግኝን መትከልና መንከባከብ ባህል እያደረገው እንደመጣ የጠቀሱት አቶ ሰይፈ በቀጣይም ተቋሙ የተተከሉ ችግኞች ያደረሱበትን ሁኔታ እየተከታተለ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ይህም ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ እያጋጠማት ያለውን ችግር ለማሳወቅና አገሪቷ ለአየር ንብረት ለውጥ እያበረከተች ያለውን በጎ አስተዋጾኦ በማዳረስ የበለጠ ስራ ለመሰራት ነው ሲሉም ተናግረዋል። በኤጀንሲው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ወንድራድ በበኩላቸው እንደተናገሩት የዜና አገልግሎት ሰራተኞች መረጃን ተደራሽ ለማድረግ ከሚያደርጓቸው ጥረት በተጓዳኝ የታሪኩ አካል ለመሆን በችግኝ ተከላው አሻራቸውን አኑረዋል። በቀጣይም ተቋሙ የተከለውን ችግኝ ከመንከባከብ ባለፈ በችግኝ ተከላና በአካባቢ ጥበቃ በጎ ስራ የሰሩ ተቋማትን፣ ግለሰቦችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን የማስተዋወቁን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የፋይናንስ ግዥና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ መንበረ እሸቱ በበኩላቸው ተቋሙ በየአመቱ ችግኝ እንደሚተክል ተናግረው  የዘንድሮን ለየት የሚያደርገው ተቋሙ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ የሚከታተልባቸውን የተለያዩ አሰራሮች መዘርጋቱ ነው ብለዋል። ቦታ የመረከብ፣ ለችግኝ የሚሆኑ ጉድጓዶችን የማዘጋጀት፣ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ሰራተኛን በቋሚነት  የመመደብና የመከታተል ስራ ለመስራት ውል መገባቱንም ተናግረዋል ወይዘሮ መንበረ። ይህም ችግኞቹ እንዲጸድቁ የሚያደርግ ስራ ለመስራትና ለመንከባከብ የሚያስችል ስራ ሆኖ ዓመቱን ሙሉ ለመስራት ያግዛልም ሲሉ ተናግረዋል። ወይዘሮ የንጉስ ውቤ የተባሉ የተቋሙ ሰራተኛም የተተከሉት ችግኞች እንዲበቅሉ ማስተባበር፣ መቀስቀስና ጊዜ መድቦ የክትትል ስራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል። በመሆኑም እንደ ዜጋ ጓደኞቼን ይዥ የመንከባከብ ስራ እሰራለሁ ሲሉም ቃል ገብተዋል። በዘንድሮ ክረምት አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ የተያዘ ቢሆንም በዛሬው እለት 200 ሚሊዮን ለመትከልና የዓለምን ክብረ ወሰን ለመስበር ችግኞች እየተተከሉ እንደሚገኝም ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም