ቀጥታ፡

"እየተተከሉ ያሉት ችግኞች ፀድቀው ለፍሬ ይበቁ ዘንድ በትኩረት ሊሰራ ይገባል" -- አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 22/2011  በአሁኑ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ህዝባዊ ተነሳሽነት እየተተከለ ያለው ችግኝ ፀድቆ የሚፈለገው ዓላማ ግቡን ይመታ ዘንድ በትኩረት መስራት ይገባል ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ገለፀ። በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዛሬ በተጀመረው ዘመቻ መሰረት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ጨምሮ የኃይሌ ገብረስላሴ የተለያዩ ድርጅቶች ሰራተኞች በሱሉልታ ከተማ ችግኝ ተክለዋል። ይህን አስመልክቶ ሻለቃ ኃይሌ ለኢዜአ በሰጠው ቃል ‘’እየተተከሉ ያሉት ችግኞች ፀድቀው ለፍሬ ይበቁ ዘንድ በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ብሏል።  ''የችግኝ ተከላ ዘመቻው ለችግኝ አቅርቦት፣ ለጉዳጓድ ቁፋሮና ሌሎች ዝግጅቶች በርካታ ወጪና የሰው ኃይል የወጣበት ነው'' ያለው ሻለቃ ኃይሌ  በከፍተኛ ህዝባዊ ተነሳሽነት እየተተከለ ያለው ችግኝ ፀድቆ የሚፈለገው ዓላማ ግቡን ይመታ ዘንድ በትኩረት መስራት ይገባል ሲልም አስገንዝቧል። እርሱ በሚያስተዳድራቸው ተቋማት ሰራተኞች የተተከሉት ችግኞች ፀድቀው ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም ሻለቃ ኃይሌ አክሎ ተናግሯል። በተለይም የአገሪቱ የስፖርት ቤተሰቦች በሱሉልታ እየተተከሉ ላሉት ችግኞች አስፈላጊውን ክብካቤ በማድረግ የሚለማመዱበትን አካባቢ ጤናማ አየር ምንጭ በማድረግ የበኩላቸውን አንዲወጡም አሳስቧል። በዛሬው እለት በተጀመረው የችግኝ ተከላ ዘመቻ በተለይ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የስፖርቱ ቤተሰቦችን፣ የኪነ ጥበብ ሙያተኞችን፣ የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እየተሳተፈ ነው። ማለዳ በጀመረውና በመላው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የችግኝ ተከላ የእስካሁን ትግበራ መሰረት ከ100 ሚሊዮን በላይ ዘልቋል። በዓለም በክብረ ወሰንነት ተመዝግቦ ያለው በህንድ በአንድ ቀን የተተከለው 66 ሚሊዮን ችግኝ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም