ቀጥታ፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለአረንጓዴው አሻራ ቀን ስነ ስርዓት ጎንደር ከተማ ገቡ

ጎንደር ኢዜአ ሀምሌ 22/2011  ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመላ ሀገሪቱ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ስነ-ስርአት ለመሳተፍ ጎንደር ከተማ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ ፕሬዚዳንቷ ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጋር በመሆን አጼ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የጎንደር ከተማና የማእከላዊ ጎንደር ዞን አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ በአቀባበል ስነ-ስርአቱ ላይ በከተማው የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች ፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የፋሲለደስ የኪነት ቡድንን ጨምሮ የከተማው የሰላምና የልማት ሸንጎ አባላት ተገኝተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ምንዝሮ በተባለው የገጠር ቀበሌ በሚገኘው የደን ስፋራ የችግኝ ተከላ ስነ-ስርአቱን ያስጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በማእከላዊ ጎንደር ዞን በዛሬው እለት አራት ሚሊዮን ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን ከ100 ሺህ በላይ ህዝብ በችግኝ ተከላው እንደሚሳተፍ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከችግኝ ተከላ ስነ-ስርአቱ በኋላም በጎንደር ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን ተዘዋውረው ይጎበኛሉ ተብሎ  ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም