ቀጥታ፡

መላው ኢትዮጵያውያን ለአረንጓዴ አሻራ ቀን መሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ሐምሌ 21/2011 መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነገ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓም በሚካሄደው የ"አረንጓዴ አሻራ ቀን" አገራዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዓላማው መሳካት እንዲተጋ ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ጥሪ አቀረበ። በነገው ዕለት 200 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀንበር በመላው ኢትዮጵያ በመትከል አገሪቱን በዓለም የክብር መዝገብ ላይ ማስፈር ይቻል ዘንድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ይህንኑ መርሃ ግብር በተመለከተ ዛሬ ከቀትር በኋላ በብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው መግለጫ ተሰጥቷል። በመግለጫው ላይ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በሰጡት ማብራሪያ በነገው እለት ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ 211 ሚሊዮን ችግኝ ተዘጋጅቷል። በእለቱ የሚተከሉት ችግኞችን የተመለከተ መረጃ በቴክኖሎጂ በተደገፈ ስርዓት የሚሰበሰብ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ካሉት አስተዳደራዊ መዋቅሮች መረጃው  የሚሰበሰበውም በየሶስት ሰዓቱ ነው ብለዋል። መረጃዎቹ የሚሰባሰቡት በቅድሚያ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 3 ሰዓት፣ ቀጥሎም ቀን በ6 ሰዓት እንደዚሁም ከቀትር በኋላ በ9 ሰዓት እና በ12 ሰዓት ይሆናል ብለዋል። በአጠቃላይ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ የተተከለውን ችግኝ የተመለከተ መረጃ እንደሚሰበሰብ ነው ሚኒስትሩ የገለፁት። በአገሪቱ የሚገኙ ዞን አስተዳደሮች በእለቱ በየ20 ደቂቃው የተደራጀ መረጃ ለፌደራል ማዕከል ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የፌደራል አካላት ደግሞ በየ30 ደቂቃው እንቅስቃሴውን የተመለከተ መረጃ ወደ መረጃ ቋት ማስገባት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል። በተጨማሪም አጭር የፅሁፍ መልእክትን በመጠቀም በቀጥታ መረጃን ማስተላለፍ እንደሚቻልም ተገልጿል። እንደሚኒስትሩ ገለጻ መረጃው ቀጥታ ወደማዕከል ከገባ በኋላ አሰራሩን በሚቆጣጠሩት ባለሙያዎች አማካኝነት ተተንትኖ ለብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ይተላለፋል። በመጨረሻም መረጃው ወደ ጽረ-ገጽና ዳታ ቤዝ የሚለቀቅ ይሆናል። ድረ-ገጹ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆኖ የችግኝ ተከላውን ሂደት መከታተል የሚያስችለው ነውም ተብሏል። ኮሚቴው እንዳለው በእለቱ ሙሉ ቀን የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ በተመለከተ አስፈላጊ መግለጫዎችና ማብራሪያዎች የሚቀርቡ ሲሆን፤ የቀጥታ የሚዲያ ስርጭትም ይኖራል። መላው ኢትዮጵያዊያን የነገው እለት ውሎ ዋነኛ የሥራ ተግባር ችግኝ መትከል መሆኑንም ኮሚቴው አስገንዝቧል። በፀጥታ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት አሻራቸውን ማስቀመጥ ይችሉ ዘንድ በፈረቃ ችግኝ እንዲተክሉ ይደረጋል ተብሏል። በርካታ ህዝብ በሚወጣባቸውና ተከላ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ትክክለኛ የችግኝ አተካከል ስርዓት እንዲኖር የሚያግዙ ባለሙያዎች መመደባቸውም ተመልክቷል። ህብረተሰቡም ችግኞቹ በአግባቡ ተተክለውና ፀድቀው ለፍሬ እንዲበቁ የባለሙያዎቹን ገለፃ ተግባራዊ በማድረግ ተከላቸውን እንዲከውኑ ኮሚቴው አሳስቧል። በተከላ ቦታዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ባህል የሚያንጸባርቁ ሁነቶች የሚኖሩ መሆኑም ተመልክቷል። የ"አረንጓዴ አሻራ ቀን" በሚል በመላው ኢትዮጵያ የሚተገበረውን የ200 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዓለም ክብረ ወሰን ሆኖ እንዲመዘገብ በተመረጡ ቦታዎች ምስክር የሚወስዱና መረጃ የሚሰበስቡ እንዲሁም መረጃውን ለማጠናቀር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁንም ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው አስታውቋል። በመሆኑም ይህ ታላቅ አገራዊ ዓላማ ግቡን እንዲመታ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና ተማሪዎችን ጨምሮ መላው ህዝብ ለአረንጓዴ አሻራ ቀን ስኬት በሙሉ አቅሙ እንዲተጋ አስተባባሪ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል። ህንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀንበር 66 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል በዓለም የክብር መዝገብ ላይ በቀዳሚነት ሰፍራ ትገኛለች፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም