ቀጥታ፡

የቀዳማዊ አፄ ሃይለ ስላሴ የመታሰቢያ ማህበር ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ሽለመ

አዲስ አበባ  ኢዜአ ሐምሌ 21 ቀን 2011 የቀዳማዊ አፄ ሃይለ ስላሴ የመታሰቢያ ማህበር ድጋፍ እያደረገላቸው ከሚያስተምራቸው ተማሪዎቹ መካከል ከፍተኛ ውጤት ላመጡት የእውቅናና የገንዘብ ሽልማት አበረከተ። በከፍተኛ ውጤት ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ለሽልማት ከበቁት 14 ተማሪዎች መካከል 7ቱ የአካል ጉዳተኞች ናቸው። ማህበሩ የቀዳማዊ አፄ ሃይለ ስላሴ 127ኛ የልደት በዓልን ትናንት ባከበረበት ስነ-ስርዓት ላይ ነው ለተማሪዎቹ ሽልማቱን የሰጠው። የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ሊቀ ካህናት አባይነህ አበበ ማህበሩ ባለፉት ዓመታት ድጋፍ አድርጎላቸው ትምህርታቸውን ካጠናቀቁት  400 ተማሪዎች መካከል 300ዎቹ  በተለያየ የስራ መስክ ተሰማርተው አገራቸውን እያገለገሉ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህ ዓመትም ድጋፍ እያደረገላቸው ከሚገኙት 28 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል 14ቱ ከፍተኛ ውጤት አምጥተው  መመረቃቸውን ተናግረዋል። ማህበሩ የገንዘብ ሽልማትና እውቅና የሰጠውም ለእነዚሁ የዘንድሮ ምሩቃን ነው ብለዋል። ከተሸላሚ ምሩቃኑ መካከል 7ቱ የአካል ጉዳተኛ መሆናቸውንም  ሊቀ ካህናት አባይነህ  አመልክተዋል። ምንም ዓይነት ረዳት ለሌላቸው ተማሪዎች ማህበሩ የገንዘብ ፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና የሞራል ድጋፍ እያደረገ ሲሆን ይህም ተማሪዎቹ  ትምህርታቸውን ያለ ችግር እንዲከታተሉ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀዋል። የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ 127ኛ የልደት በዓልን በተመለከተ በተከናወነው ስነ-ስርዓት ላይ እንደተገለፀው ንጉሱ አገሪቱን ባስተዳደሩባቸው ዓመታት ዘመናዊ ትምህርትን ማስፋፋትን ጨምሮ ያበረከቷቸው ማህበራዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ፖለቲካዊ አስተዋፅኦዎች ተወስተዋል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ-ጥር የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእርሳቸው  ዘመነ መንግስት የተመሰረተ ተቋም መሆኑም ተነስቷል። ኢትዮጵያ በአለም እንድትታወቅ፤ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት እንዲወጡና  ህብረት እንዲፈጥሩ ሚና ከተጫወቱት ሰዎች መካከል መሆናቸውም ተነግሯል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም