አገር የሚለማው ግብርን በታማኝነት በመክፈልና በዜጎች ጥረት ነው - ተሸላሚ ግብር ከፋዮች - ኢዜአ አማርኛ
አገር የሚለማው ግብርን በታማኝነት በመክፈልና በዜጎች ጥረት ነው - ተሸላሚ ግብር ከፋዮች
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 21/2011 ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገር በዜጎች ጥረት እንጂ በልመናና ብድር እንደማይለማ ተገንዝቦ ግብሩን በታማኝነት መክፈል አለበት አሉ ተሸላሚ ግብር ከፋዮች። ተሸላሚዎቹ የተሰጣቸው ዕውቅና አገራዊ ግዴታዎችን የመወጣት ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸውም ተናግረዋል። የገቢዎች ሚኒስቴር በ2011 ዓ.ም ግብር በታማኝነት ለከፈሉ ግለሰቦች ትናንት ምሽት በብሔራዊ ቤተ መንግስት የምስጋናና ዕውቅና ዝግጅት አካሄዷል። በስነ-ስርዓቱ በአገር ውስጥ ገቢ እና በጉምሩክ ክፍያ የተመደቡ 165 ግብር ከፋዮች እንደ አፈጻጸማቸው በፕላቲኒየም፣ ወርቅና ብር ደረጃ ተሸልመዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ሞተርና ኢንጂነሪንግ ኩባንያ (ሞኤንኮ) በአገር ውስጥ ገቢ፤ ትራኮን ትሬዲንግና ትራንስ ኢትዮጵያ ደግሞ በጉምሩክ ምድብ በፕላቲኒየም ደረጃ ከተሸለሙ ድርጅቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሸላሚ ግብር ከፋዮች እንደሚሉት፤ ግብርን መክፈል ለአገር ብልጽግና አሻራን አንደማኖር የመቁጠሩ ባህል ይበልጥ ሊጎለብት ይገባል። የኢትዮጵያ ታነሪ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጸደንያ መክብብ "የቢዝነስ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ትርፍ ላይ ብቻ ትኩረት ስለሚያደርጉ ግብር መክፈልን እንደ ጫና ይመለከቱታል" ብለዋል። ነገር ግን ትርፍ ማግኘትና ግብርን መክፈል ጎን ለጎን አብረው መሄድ እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። አገር የሚበለጽገው ግብራቸውን በታማኝነት በሚከፍሉ ዜጎች እንጂ በልመና እንዳልሆነ በመጠቆም። የመቀሌ ፋርም ባለቤት አቶ ህንጻ ሃጎስ በበኩላቸው የአንድ አገር ኢኮኖሚ ራሱን ችሎ የሚቆመው ግብር በትክክል መሰብሰብ ሲቻል ነው ይላሉ። በመሆኑም "ድርጅቴ ግብርን በታማኝነት የመክፈሉን ኃላፊነት አጠናክሮ ይቀጥላል" ነው ያለት። "ግብርን በመክፈል ዙሪያ የነበሩ ህገ-ወጥ ድርጊቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ መጥተዋል" ያሉት ደግሞ የያሬድ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ኃላፊ አቶ ያሬድ ጥሩነህ ናቸው። ሁሉም ዜጋ ግብሩን በትክክል መክፈል ከቻለ መንግስት ከዘርፉ አገኘዋለሁ ብሎ ካቀደው ገንዘብ በላይ መሰብሰብ እንደሚቻልም ይናገራሉ። ከዚህ አንጻር የገቢዎች ሚኒስቴር ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት በመጠቆም። የገቢዎች ሚኒስቴር በ2011 በጀት ዓመት 192 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ከግብር መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ13 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። መስሪያ ቤቱ በተያዘው የበጀት ዓመት 248 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙም ይታወቃል።