ቀጥታ፡

በጋምቤላ በአረንጓዴ አሻራ ቀን ከ300 ሺህ በላይ ችግኞች ይተከላሉ

ጋምቤላ ኢዜአ ሐምሌ 21 ቀን 2011 በጋምቤላ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከ300 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቱ መጠናቀቁን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ። ሕዝቡ ለመርሐ ግብሩ መሳካት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠይቋል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኮይት ሉል ለኢዜአ እንደገለጹት በመርሐ ግብሩ 130 ሄክታር መሬት በደን ይሸፈናል። በአሁኑ ወቅት ችግኞች ወደሚተከሉባቸው ቦታዎች መጓጓዛቸውን ገልጸዋል። ተከላው ከሚከናወንባቸው ሥፍራዎች መካከል በጋምቤላ ከተማ አቅራቢያ 120 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም አስረድተዋል። በመርሐ ግብሩ ከ27 ሺህ በላይ የክልል፣ የፌደራል መንግሥት ተቋማትና የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች  መሳተፋቸውን ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል። በመርሐ ግብሩ የሚተከሉትን ጨምሮ በዘንድሮው ክረምት ከ2 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በጥላ፣ በፍራፍሬና በሮዶስ ሳር ለማልበስ እየተሰራ መሆኑን አቶ ኮይት ገልጸዋል። የክልሉ ሕዝብ በዕለቱ በነቂስ በመውጣት መርሐ ግብሩን ስኬታማ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በሌላ በኩል የጋምቤላ - ኢሊያ የመንገድ ፕሮጀክት ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ ቀን በማስመልከት ትናንት የችግኝ ተከላ አካሂደዋል። የፕሮጀክቱ አማካሪ ኢንጀነር ሐብታሙ አስጨናቂ እንዳሉት ቀኑን በማስመልከትና በፕሮጀክቱ የጠፋውን ደን ለመተካት ስምንት ሺህ ችግኝ እየተተከለ ነው ብለዋል። ችግኞች መተካለቸው ብቻ ግብ ስለማይሆን እንክብካቤ የሚያደርግላቸው  የሰው ኃይል መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ደን ከሰው ሕይወት እስትንፋና ምግብ ጋር ተያያዥነት እንዳለው በመገንዘብ በልማቱ ሁሉም ተሳታፊ ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው በችግኝ ተከላው የተሳተፉት አቶ ፈቃደኢየሱስ ፍሥሐ ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም