የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ውጤት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ውጤት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2011 በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የነበረው 2ኛው የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ውጤት ይፋ ሆነ:: ባለፉት ስድስት ወራት በአገር ውስጥ ባለሙያዎች በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከቀረቡ 159 ሆቴሎች መካከል ለደረጃ ምደባው 88ቱ ተለይተው ነበር ፡፡ በዚህም በዓለም ዓቀፍ የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ከ88ቱ ውስጥ 83ቱ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ኮከብ አግኝተዋል፡፡ ደረጃ ካገኙት መከል በአዲስ አበባ 30፣ በአማራ ክልል 12፣ በኦሮሚያ ክልል 12፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል 10፣ በትግራይ ክልል 8፣ በቤኒሻንጉል ክልል፣ 3 በድሬዳዋ 2 እንዲሁም በጋምቤላና በሀረር አንድ አንድ ሆቴሎች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ምደባ አግኝተዋል፡፡ ከሱማሌ የቀረበ አንድ ሆቴል ከደረጃ በታች መሆኑም ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ 12 ባለ አራት፣ 13 ባለ ሶስት፣ 31 ባለሁለት እንዲሁም 27 ባለ አንድ ኮከብ ደረጃ ነው ለሆቴሎቹ የተሰጠው፡፡ ከእነዚህ መካከል በአዲስ አበባ 6 ባለ አራት፣ 4 ባለ ሶስት ሲሆኑ፤ በአማራ 3 ባለ አራት ሁለት ባለ ሶስት እንዲሁም በኦሮሚያ 2 ባለሶስት ኮከብ ደረጃ ተለይተዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሣው የይፋ ማድርጊያ መድረክ ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልዕክት ባለንበት ዘመን በሆቴል ዘርፍ የገበያ ውድድር በተሻለ ሁኔታና ለእንግዶች የተመቸ አገልግሎት በመስጠት ዙሪያ ብዙ ጥረትና ትግል ይፈልጋል ብለዋል፡፡ በጥራትና በብቃት የተሰማራ የሰው ኃይልን ይዞ፣ የተሻለ የመስተንግዶ አገልግሎት በመስጠት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ቁመና ላይ መገኘት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ የድርጅቶችንና የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባት እንደሚያስችልም ገልፀዋል፡፡ ሚኒስቴሩም ሆቴሎች ካላቸው ደረጃ ወደኃላ እንዳይመለሱ የሚያደርገውን ቁጥጥርና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል ሚኒስትሯ፡፡ በ2007 ዓ.ም. በተደረገው የመጀመሪያ ዙር የሆቴሎች ደረጃ ምደባ 250 ሆቴሎች ከ1ኛ እስከ 5ኛ ደረጃ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ በዘርፉ ከታዩት ተግዳሮቶች መካከል የንፅህናና የውበት ችግር የአስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች አለመሟላት፣ የሠለጠነ የሠው ኃይል ጉድለት የማስፋፊያው ቦታ ችግር እና የቅንጅታዊ አሠራር ጉድለት ተጠቅሰዋል፡፡ የተቀሩት የኮኮብ ደረጃ እናይሰጣቸው ምከንያት ከሆኑት መካከልም ደረጃን ለመመደብ የማይመጥኑ መሆናቸው፣ በቅርብ ጊዜ መሠራታቸውና ባለሆቴሎች ፍቃደኛ አለመሆናቸው እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡