በድሬዳዋ አስተዳደር 200ሺህ ችግኝ በአንድ ቀን ለመትከል ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አስተዳደር 200ሺህ ችግኝ በአንድ ቀን ለመትከል ተዘጋጅቷል
ድሬደዋ ኢዜአ ሐምሌ 20 /2011 በአረንጓዴ አሻራ ቀን በድሬደዋ አስተዳደር 200ሺህ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አስታወቁ። ምክትል ከንቲባው አቶ አህመድ መሃመድ ችግኝ በተከሉበት ወቅት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በተያዘው ክረምት በድሬደዋ ገጠር እና ከተማ ከ871 000 በላይ ችግኞች ይተከላሉ፤ በእስካሁኑም ከ30ሺህ በላይ ችግኖች ተተክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አብይ አህመድ በሀገር አቀፍ ደረጃ 4 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል የነደፉትን እቅድ ለማሳካት በድሬዳዋም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በመጪው ሐምሌ 22 ቀን ብቻ ገጠርና ከተመማ ጨምሮ በአስተዳደሩ ውስጥ በተመረጡ ዋና ዋና ሥፍራዎች 200ሺህ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ችግኝ ተክሎ ማሳደግ ለድሬዳዋ ባህል ነው፤ የህልውና ጉዳይ ነው፤ ከጎርፍ ስጋት ይከላከላል፤ ሞቃታማውን አየር ለህይወት ተስማሚ ያደርጋል “ ብለዋል ፡፡ የድሬዳዋ ነዋሪ በሙሉ በክረምቱ በግቢው ባለው ቦታ ጭምር የሚችለውን ችግኝ በመትከል ተንከባክቦ አረንጓዴ የለበሰች ድሬደዋን ለትውልድ የማስረከብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአስተዳደሩ የአካባቢ ደን አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ አብዱ መሀመድ በበኩላቸው “እንደ ከአሁን ቀደሙ ችግኞች ተክሎ ዞር ብሎ አለማየት አይቻልም ፤ የሚተከሉት ችግኞች በሙሉ ባለቤት ይኖራቸዋል “ ብለዋል፡፡ ችግኖችን ተክሎ ማሳደግ ድሬዳዋ ከጎርፍ አደጋ መከላከል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአስተዳደሩ ግብርና ፣ውሃ ማእድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው። በተለይ በገጠር እየተተከሉ የሚገኙ ፍራፍሬ ዛፎች አርሶ አደሩን ምርታማነት የሚጨምሩና የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡ ሐምሌ 22 ለሚተከሉት ችግኖች ጉድጓዶች ተዘጋጅተዋል ተብሏል። በዳዊት ለአረጋውያን መርጃ መዕከል ችግኝ ሲተክሉ የነበሩት የ70 ዓመቱ አዛውንት አቶ አለሙ ረጋሳ “ድሬዳዋ ያለ ዛፍ ጥላ በረሃ ናት፤ ጎርፍና ንዳድም የሚያጠቃት በመሆኑ ይህን ለመከላከል 4 ዛፍ ተክያለሁ ፤ እስኪያድጉ እንከባከባቸዋለሁ “ብለዋል፡፡ አርሶአደር አደም አህመድ “ባለፈው ሣምንት በእርሻዬ ውስጥ 10 የፓፓዬ፣ 30 የብርቱኳንና የማንጎ ችግኞች ተክያለሁ ፤ ችግኞቹን ተንከባክቤ በማሳደግ ገቢዬ እንዲጨምር እየሰራሁ ነው “ብለዋል፡፡ በሐምሌ 22 በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ብቻ 10 ሺ ችግኞች እንደሚተከሉ ዩኒቨርስቲው ገልጿል። የዩኒቨርስቲው የአለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሪት መቅደስ ካሳሁን “ለተከላው የሚሆኑ ችግኞችና ጉድጓዶች ጨምሮ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ናቸው “ብለዋል፡፡