ስታር አሊያንስ የመንገደኞቹን በረራ የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ የባዮሜትሪክ መረጃ ቅብብሎሽ 'ኔክ' ከተባለ አለም አቀፍ የኢንፎርሜሸን ኩባንያ ጋር ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
ስታር አሊያንስ የመንገደኞቹን በረራ የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ የባዮሜትሪክ መረጃ ቅብብሎሽ 'ኔክ' ከተባለ አለም አቀፍ የኢንፎርሜሸን ኩባንያ ጋር ተፈራረመ
ሐምሌ 20/2011 (ኢዜአ) በአለም ግዙፍ የሆነው የአየር መንገዶች ትስሰር ስታር አሊያንስና በአይቲ ዘርፍ ቀዳሚ የሆነው ኔክ ኮርፖሬሽን የተፈራረሙት የባዮሜትሪክ መረጃ የማንነት መለያ መደላድል ስምምነት በስታር አሊያንስ አባል አየር መንገዶች ተደጋጋሚ በረራ ለሚያደርጉ ደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ተብሏል። ስምምነቱ የሁለቱን ተቋማት ስትራቴጂክ ግብ እና የደንበኞቹን ጉዞ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስጉዝ ከመሆኑ ባለፈ በበረራ ዘርፉ ያለውን ታማኝነት የሚያጎለብት እንደሆነ በጀርመን ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ተገልጿል።
ደንበኞቹ አንድ ጊዜ በመረጃ ቋቱ ውስጥ ስማቸው ከሰፈረ ከዚህ ቀደም ፓስፖርት የሚጠይቁ አገልግሎቶችን ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ፓስፖርት ሳይጠየቁ እንዲያገኙ ይደረጋል።
አገልግሎቱ የፊት ገጽታን በሚያነብ ቴክኖሎጂ የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል
ከአገልግሎቶቹ መካከል ሻንጣ ማውጣት፣ ካፌ መጠቀምና የፍተሻ ቦታዎችን ማለፍ ይጠቀሳሉ።
መደላድሉ በተጨማሪ አየር ማረፊያዎችና የስታር አሊያንስ አባል የሆኑ አየር መንገዶች የአገልግሎት ብቃታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።
አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉት ደንበኞች በተደጋጋሚ በረራ የሚያደርጉና የባዮሜትሪክ መረጃ ቋቱን ለመጠቀም ፈቃድ የሚሰጣቸው ብቻ ናቸው።
የግል መረጃው የሚታየው ተጓዥ ሲስማማ ብቻ መሆኑም ተገልጿል። አገልግሎቱን የሚያገኘው ደንበኛ ለደህንነትና ለኢሚግሬሽን ህግ ሲባል ፓስፖርቱን እንዲያሳይ ሊጠየቅ እንደሚችልም ተጠቁሟል።
የስታር አሊያንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፈሪ ጎህ “መንገደኞቻችን ከስህተት ነጻ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ ከጠንካራ አጋር ጋር ተፈራርመናል። ድርጅታችን ደንበኞቹ ምቹ ጉዞ እንዲኖራቸው ቁርጠኛ ሲሆን ኔክም ይህንን ፍላጎታችንን በእጅጉ ያሳካልናል” ብለዋል።
የኔክ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ታካሺ ኒኖ በበኩላቸው ”ከስታር አሊያንስ ጋር አብረው መስራታቸው እንደሚያስደስታቸውና የፊት ገጽታን የሚያነበው ቴክኖሎጂ ለአየር መንገዶች አዲስ ነው'' ብለዋል።
ደህንነቱ አስተማማኝ እንደሆነ የተገለጸው ቴክኖሎጂ ቀደም ብሎ በአሜሪካ፣ ሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግና በጃፓን ስራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል።
ሁለቱ ተቋማት የመጀመሪያውን የባዮሜትሪክ መረጃ አገልግሎት እኤአ በ2020 የመጀመሪያ ሩብ አመት በስታር አሊያንስ አባል አየር መንገዶች አየር ማረፊያ ተግባራዊ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
የስታር አሊያንስ ትስስር እኤአ በ1997 የተመሰረተ ሲሆን አለም አቀፍ እውቅና፣ ተደራሽነትና ከስህተት የነጻ አገልግሎት ለደንበኞቹ እንደሚሰጥም በመግለጫው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አባል የሆነበት ስታር አሊያንስ በየእለቱ 19 ሺህ በረራዎችን በማድረግ በ1 ሺህ 300 አየር መንገዶችና በ194 አገሮች አገልግሎቱን ይሰጣል።