ተቋማቱ ባለፉት ዓመታት በሰሩት የአረንጓዴ ልማት የደን ክልል መፍጠራቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ ባለፉት ዓመታት በሰሩት የአረንጓዴ ልማት የደን ክልል መፍጠራቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2011 የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ዓመታት በሰሩት የአረንጓዴ ልማት የደን ክልል መፍጠራቸውን ገለጹ፡፡ ተቋማቱ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ቅድመ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ተቋማቱ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት የችግኝ ተከላ ተሳትፎ የራሳቸውን የደን ክልል መፍጠር ችለዋል። በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የችግኝ ተከላ አስተባባሪዋ ወይዘሮ ትዝታ ደጀኔ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ባለፉት 11 ዓመታት ከተጠሪ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የአረንጓዴ ልማትን በመደበኛ እቅድ ይዞ በተለያዩ ስራዎች ችግኝ ሲተክልና ደን ሲያለ ቆይቷል፡፡ ዘንድሮም በሃገር አቀፍ ደረጃ ለተያዘው እቅድ 900 ያህል ሰራተኞችን በማሳተፍ 7 ሺህ ችግኝ ለመትከል ግራር ጃርሶ ወረዳ ወርጦ የሚባል አካባቢ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቦታ መረከባቸውንና የሚኒስቴሩ መሆኑን የሚገልፅ ታፔላ ማኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ትዝታ ገለጻ፤ ባለፉት አመታት በድሬ ግድብ ዙሪያ 12 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በሚኒስቴሩ የተተከለው ችግኝ ለደን ክልልነት በቅቷል። በአዲስ አበባ በተለምዶ ሲ ኤም ሲ በመባል በሚታወቀው ሞዴል የአረጋውያን አካባቢ በጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኝ በዛፍ የተሸፈነ አረንጓዴ ቦታ መኖሩን ጠቅሰው፤ በኦሮሚያ ሰበታ ሃዋስ ወረዳ ከ 6 ሺህ በላይ ችግኞች በሚኒስቴሩ መተከላቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ሜታ አቦና በሆጨጫ ተራራ 7 ሺህ ችግኞች፣ በድል በር አካባቢ ሶስት ሺህ ችግኞችና በዚህ አመት ሀምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ሁለት ሺህ ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል፡፡ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የችግኞችን ሁኔታ የሚከታተል ባለሙያ እንዳለው የገለጹት ወይዘሮ ትዝታ፤ ከዛፈ ችግኝ መረጣ ጀምሮ ተተክለው እስኪፀድቁ ድረስ በጀት ተመድቦ ክትትል እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ በአመት ሁለት ግዜ ለዚሁ ስራ የተቋቋመ ኮሚቴ የችግኞቹን ሁኔታ እንደሚጎበኝ ተናግረው፤ በተለይ በፀሃይ ወቅት ውሃ እንዲያገኙና የማድረግ፣ የመኮትኮትና የመጽደቅ ስጋት ያጋጠማቸውን ችግኞች የመተካት ተግባር እንደሚከናወን አመልክተዋል። “ችግኝ እንደ ልጀ ማለት ነው፣ ከተንከባክበን ከያዝነው አድጎ ይጠቅማል” ያሉት ወይዘሮ ትዝታ የበጋውን ወቅት እስኪወጡና እስኪያድጉ መንከባከብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የችግኝ ተከላ አስተባባሪ ወይዘሮ እታገኝ ተካልኝ እንዳሉት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅቱ በየአመቱ 2 ሺህ 500 ችግኝ ሲተክል መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በ2011 ዓ.ም የክረምት ወቅት ብቻ በተያዘው የአራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ በመሳተፍ ለአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ድርጅቱ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ወይዘሮ እታገኝ ገልጸዋል። “ድርጅቱ በጥቅሉ እስካሁን የዘንድሮውን ጨምሮ 26 ሺህ ችግኝ እንደተከለ አውስተው ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ድልበር እግዜአብሄር አብ አካባቢ ችግኝ ለመትከል የሚያስችል ጉድጓድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደቆዩ የተናገሩት ሲስተር ረሚላ አህመድ በበኩላቸው ''እንደ መንግስት ሰራተኛ ከልማትና አገርን ከመጥቀም አንፃር ግንባር ቀደም ስራ ይጠበቅብናል'' ብለዋል። “አሁን ላይ የምንሰራው አረንጓዴ ልማት ለጤናም ጠቃሚ ነው” ያሉት ሲስተር ረሚላ፤ በአየር ብክለት በተለይ ህፃናት ከላይኛው የመተንፈሻ አካል ህመም ጋር በተያያዘ ተጎጂ እንዳይሆኑ ለመከላከል የሚያስችል ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል። በድርጅቱ የተተከሉ ችግኞች ከ90 ከመቶ በላይ መፅደቃቸውንና በተለይ በአዲስ አበባ ወደ ዛፍነት ያደጉት ከኢንዱስትሪና ከመኪና የሚመነጨውን ካርቦን በመቀነስ የአየር ብክለትን ደረጃ በመቀነስ በጎ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ሲስተር ረምላ ተናግዋል። ሁለቱም ተቋማት በተለይ ችግኝ በሚተከልባቸው አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮችና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች የሚያደርጉትን እገዛ እና እንክብካቤ አድንቀዋል ምስጋናም አቅርበዋል፡፡