በምስራቅ አፍሪካ የቼስ ውድድር እየተሳተፉ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አሸንፈዋል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አፍሪካ የቼስ ውድድር እየተሳተፉ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አሸንፈዋል
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 በጅቡቲ እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድር እየተሳተፉ የሚገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተወዳዳሪዎች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አሸንፈዋል። በአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው ውድድር ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም በጅቡቲ መጀመሩ ይታወቃል። ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮጵያውን ተወዳዳሪዎች በመጀመሪያ ጨዋታቸው ድል ቀንቷቸዋል። በወንዶች ለይኩን መስፍን የጅቡቲውን አብዲላሂ ሳላህ አቢሲሊያን እንዲሁም አይዳኙም ግዛቸው የጅቡቲውን መሐመድ ሙሐመድን አሸንፈዋል። በሴቶች ፌቨን ገብረመስቀል የጅቡቲዋን ዲሬህ መሐመድን አሸንፋለች። ሶስቱ ተወዳዳሪዎች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በማሸነፋቸው አንድ አንድ ነጥብ አግኝተዋል። በወንዶች በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች የኡጋንዳው ክዋሚ ፓትሪክ ኢትዮጵያዊውን እንዳለ መኮንን ያሸነፈ ሲሆን በዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ባንዲራ የሚወዳደረው አብዲ ራሂም ሌላኛውን ኢትዮጵያዊ ኤርሚያስ ተክለማርያምን ረቷል። በሴቶች በተካሄደ ሌላ ጨዋታ የጅቡቲዋ ኤልሚ ራማህ ኢትዮጵያዊቷን ልደት አባተን ማሸነፍ ችላለች። በቼስ የውድድር ህግ መሰረት የውድድር አሸናፊ የሚለየው የቼስ ተወዳዳሪው በዙር ከተጋጣሚዎቹ ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በሚሰበስበው ነጥብና ባሸነፈው የጨዋታ ብዛት አማካኝነት ነው። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያኑን ጨምሮ የሌሎች አገራት ተወዳዳሪዎች ቀጣይ የዙር ጨዋታዎችን እርስ በእርስ የሚያደርጉ ይሆናል። ዛሬ በሴቶች ውድድር በወጣው መርሃ ግብር ፌቨን ገብረመስቀል ከልደት አባተ ጋር የሚጫወቱ ሲሆን በወንዶቹም የቀጣይ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ የሚካሄዱ ይሆናል። የምስራቅ አፍሪካ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድር እስከ ሰኔ 12 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።