ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ
አምቦ ሐምሌ 19 / 2011 የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ኅብረተሰብ አሳታፊ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዓመታዊ መድረክ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር ሂደት፣በተማሪዎች የተግባር ልምምድ፣ በምርምር ማህበረሰብ አገልግሎትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች ያሉትን ችግሮችን፣ የመፍትሄ ሃሳቦችና በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የሚሰራባቸውን የማህበረሰቡን ችግሮች ለመለየት እንደሚጠቀምበት ተገልጿል፡፡ እንዲሁም በቴክኖ ኤክስፖ ዘርፍ በሚቀርቡት ከቴክኖሎጂ ጋር ለመተዋወቅና በቴክኖሎጂ ሽግግር የትኩረት አቅጣጫ ለማመላከት እንደሚያስችል ተመልክቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ማህረሰብ አገልግሎትና ቷቋማዊ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ብዙነሽ ሚደክሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ዘርፍ ተጠቃሚዎችን ያማከሉ ችግር ፈቺ ሥራዎች ለማከናወን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአገሪቱ ተፈላጊ የሆኑ ሙያና ፈጠራን ያካተተ ስልጠና በመስጠት ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎች ለመፍጠር እያሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ እንዲሁም ፍትሃዊና ጥራት ያለው የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት የአገሪቱን የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላትና የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት ለማርካት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በጀት በዚህ ዓመት ብቻ 59 ምርምር 40 የማህበረሰብ አገልግሎትና 11የቴክኖሎጂ ሽግግር ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በተጨማሪም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍ አራት ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ምክትል ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል። እንዲሁም ዘጠኝ የምርምር ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ተጠቃሚ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ መድረኩን ሲከፍቱ በመድረኩ የተካተተው የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በዝግጅቱም ሆነ በአቀራረቡ ለዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያውእንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በመድረኩ ከ50 በላይ ተቋማት የሚሳተፉ ሲሆን፣ ከ40 በላይ የማሽነሪና የሶፍትዌር ፈጠራዎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች፣የሲቪክ ማህበራት፣ከግል ዘርፍና ከማህበረሰቡ የተውጣጡ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2011 የትምህርት ዘመን በ70 የቅድመ ምረቃና በ52 የድሀረ ምረቃ ፕሮግራሞች 26ሺህ 573 ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በክረምትና በተከታታይ ትምህርት አስተምሯል፡፡