የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር ከመንግስት ጋር እንደሚሰራ ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር ከመንግስት ጋር እንደሚሰራ ገለፀ
ሐምሌ 19/2011 የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር በአገራዊ አንድነትና ልማት ጉዳዮች ከመንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገለፀ። ማህበሩ ከ250 ሺህ በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ማድረጉንም አመልክቷል። ማህበሩ ኤርትራን ጨምሮ ከ50 በላይ ቅርጫፍ ያለው ሲሆን መንግስት ለማህበሩ የሰጠውን ህጋዊ እውቅና እና ክብር ተቀብሎ በአገራዊ አንድነትና ልማት ላይ ከመንግስት ጎን ሆኖ እንደሚሰራ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል። የማህበሩ ፕሬዘዳንት ሻለቃ ብርሃኑ አማረ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት ማህበሩ እውቅና ተነስቶት ህዝብንና አገርን ማገልገል እንዳይችል ሆኖ ቆይቷል። አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በሰጠው ፈቃድ መሰረት ግን ማህበሩ በ2011 ዓም የተቋቋመ ሲሆን በየቦታው የተበታተነውን የሰራዊት አባላት በማሰባሰብ ጠንካራ ማህበር ለመሆን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል። አባላቱ ያላቸውን ልምድና እውቀት በመጠቀምም ኢትዮጵያ የተሻለች አገር ሆና እንድትቀጥል እንደሚሰራም ተናግረዋል። ማህበሩ ህይወታቸውን ያጡ የሰራዊት አባላት ታሪክ እንዲታወስ ከማድረግ ባሻገር የአካል ጉዳት የደረሰባቸውንና ወላጀቸውን ያጡ ቤተሰቦችን ለመንከባከብ የሚሰራ መሆኑን ሻለቃ ብርሃኑ ገልፀዋል። የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ታመነ አባተ በበኩላቸው ማህበሩ የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆኑን ጠቅሰው ማህበራቸው የኢትዮጵያ እንድነት እንዲጠናከር፣ ዜጎቿም በመቻቻል በሰላም ይኖሩ ዘንድ የበኩሉን ለመወጣት የተቋቋመ መሆኑን አስረድተዋል። ከእንድ ሚሊየን በላይ አባላት ያሉት ማህበሩ ከሌሎች ማህበራት ጋር የመስራት ፍላጎት እንዳለውም ተናግረዋል። መንግስት አረጓዴ አሻራ ለማስቀመጥ በጀመረው መርሃ ግብር መሰረትም ማህበሩ ከ250 ሺህ በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል። ማህበሩ እንዲቋቋም ትብብር ላደረጉ የፌደራል መንግስት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሌሎች አካላት ምስጋና አቅርበዋል።