ለአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ቀን በመሳተፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችውን በኢሉአባቦር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ለአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ቀን በመሳተፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችውን በኢሉአባቦር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ
ሀምሌ 19/2011 ለሀገር አቀፉ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ቀን በንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በኢሉአባቦር ዞን በቾ እና ቢሎ ኖጳ ወረዳዎች አርሶ አደሮች ተናገሩ። በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ ቀን 14 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ቀን ለመትከል ዝግጅት መደረጉም ተመልክቷል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በወረዳዎቹ በመዘዋወር ለአረንጓዴ አሻራ ቀን እየተደረገ ያለውን የችግኝ ተከላ ዝግጅት በተመለከተበት ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች እንዳሉት በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው በግላቸው ቢያንስ እስከ መቶ ችግኞችን ለመትከል ጉድጓዶችን አዘጋጅተዋል። በበቾ ወረዳ ፉጎ የሳርዶ ቀበሌ አርሶአደር ደሳለኝ አረጋ ከሌሎች 180 አርሶአደሮች ጋር በመሆን በሚኖሩበት አካባቢ ከ10ሺ በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን ቆፍረው እለቱን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። “የችግኝ ጉድጓዱን የቆፈርነው ህዝቡን አስተባብረን ነው ፤በሐምሌ 22 አረንጓዴ አሻራ ቀንም እንዲሁ ህዝቡን እስተባብረን እንሰራለን” ብለዋል። በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው በንቃት በመሳተፍ በግላቸው እስከ 100 ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ የቀበሌው አርሶአደር ወይቱ ቶላ ናቸው። “ ወጣቶች በክፍተኛ ተነሳሽነት ችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን ቆፍረው አዘጋጅተዋል ፤እኛ ሴቶች ደግሞ በተከላው በከፍተኛ ተነሳሽነት እንሳተፋለን “ ብለዋል። በቢሎ ኖጳ ወረዳ የዲዚ ቀበሌ አርሶአደር ጎበና ሙለታ በበኩላቸው ሐምሌ 22 በግልና ከሌሎች አርሶአደሮች ጋር በጋራ የሚተክሉትን አብረው በመጠበቅ ለመንከባከብ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል። የኢሉአባቦር ዞን ቡና፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ለገሰ እንደገለጹት የመቱ ከተማን ጨምሮ በዞኑ 13 ወረዳዎች በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው 14 ሚሊዮን የሚሆኑ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል። በዕለቱ በ265 ቀበሌዎች ውስጥ ፣በትምህርት ቤቶች፣ በእምነት ተቋማት፣ በተራቆቱ አካባቢዎች እንዲሁም በዋና ዋና መንገዶች ዳርቻ ችግኞችን ለመትከል ጉድጉዶች ተቆፍረው ተዘጋጅተዋል። በዞኑ በመደበኛው መርሀግብር ደግሞ ከ134ሺ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ከ84 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው አመልክተዋል። እስካሁንም ከ60 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ከ79ሺ ሄክታር በላይ መሬት ላይ መተከሉን አስታውቀዋል።