በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 225 የውጭ ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው በኢትዮጵያ ሥራ ጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 225 የውጭ ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው በኢትዮጵያ ሥራ ጀምረዋል
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 19/2011 ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው መስክ ባከናወነችው የማስተዋወቅ ተግባር 225 የውጭ ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው በአገሪቱ ሥራ መጀመራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በመግለጫው ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዋነኛ ማጠንጠኛ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መሆኑን ጠቅሰው በበጀት ዓመቱ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅ የሚበረታታ ተግባር መከናወኑን አመልክተዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በበጀት ዓመቱ 168 የቢዝነስ መድረኮች መዘጋጀተውንና አብዛኛቹ መድረኮች በውጭ አገራት የተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ኢንቨስትመንቱን የማስዋወቅ ስራው በስፋት የተከናወነው በሚሲዮኖች በኩል ነው ብለዋል። በዚህ አማካኝነትም 1 ሺህ 150 ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የኢንቨሰትመንት ሁኔታ ለመመልከት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ አገሪቱ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል። ከነዚህም መካከል 159 የሚሆኑት ሰፊ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ፤ ከፍተኛ የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ግዙፍ ኩባንያዎች መሆናቸውን ዶክተር አክሊሉ ገልፀዋል። በአጠቃላይ በጀት ዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ውስጥ 225 ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውንና ቀሪዎቹም በቀጣይ ጊዜያት ወደ ስራ እንደሚገቡ ተናግረዋል። የግብርና ማቀነባበሪያ (አግሮ ፕሮሰሲንግ)፣ የመድሐኒት ምርቶች፣ ኢነርጂ እና ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎቹ ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል። የአገሪቱን ኢንቨስትመንት በማስተዋወቅ የተገኘው ስኬት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተናጠል ጥረት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና አጋር አካላት ድርሻም እንዳለበት አመልክተዋል። በተያያዘም በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ረገድ በበጀት ዓመቱ በተዘጋጁት የቢዝነስ መድረኮች የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችም በሽርክና መስራት የሚያስችላቸውን ትስስር እንዲፈጥሩ መደረጉንም ተናግረዋል። የተለያዩ ኩነቶችን በማዘጋጀት የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ፣ አምራችና ላኪን የማገናኘት ተግባራት ተከናውነዋል ፤ ሌሎች አገራትም ኢትዮጵያን እንዲያስተዋወቁ የሚያስችል ሥራ ተሰርቷል ሲሉ ነው ሚኒስትር ዲኤታው የገለፁት። በሌላ በኩል በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መብታቸው እንዳይጣስና ጥቅማቸው እንዳይጎዳ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አክሊሉኃይለሚካኤል አስታውቀዋል። በዚህ አማካኝነትም በተለያዩ አገራት በእስር ላይ ከሚገኙ ዜጎች መካከል 27 ሺህ 704 ከእስር ተፈተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደርጓል። በተለያዩ አገራት ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ ከሌላቸው ዜጎች ውስጥም 112 ሺህ 615 ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ጠቁመዋል። በድምሩ 140 ሺህ 319 ዜጎች ወደ ኢትዮጵጵያ መመለሳቸውንና ለዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማት አስፈላጊውን ትብብር ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አገራት በሚገኙ እስር ቤቶች ከ4 ሺህ በላይ ኢትዮጵያን እንደሚገኙ ያመለከቱት ዶክተር አክሊሉ እነርሱንም በማስፈታት ረገድ መንግስት አስፈላጊውን ተግባር እያከናወነ ነው ብለዋል። ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎችን የተመለከተውን ችግር ለመፍታት ዋነኛው መፍትሄ ዜጎችን በህጋዊ መልኩ ወደ ሌሎች አገራት መላክ እንደሆነም አክለዋል። ከዚህ አኳያ በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ አገራት ጋር የስራ ስምሪት ስምምነት መፈረሙን ተናግረዋል። ከተፈረሙት ስምምነቶች በተጨማሪ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ዜጎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመጓዝ ከጅቡቲ ተነስተው የሚጠቀሙበትን ምስራቃዊ መስመር ለማዘጋት ከጅቡቲ ጋር ውይይት እየተደረገ ነውም ብለዋል። እስረኞችን ማስፈታት መፍትሄ እንደማይሆን የገለጹት ሚኒስትር ዴታው፤ በዚህ ረገድ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት። በኢኮኖሚና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲው መስኮች የሚከናወኑ ተግባራትን በማጠናከር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አመልክተዋል።