ቀጥታ፡

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን የመልሶ ማልማትና እንክብካቤ ስራ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበበባ ኢዜአ ሀምሌ 19/2011  የሰሜን ተራሮዎች ብሄራዊ ፓርክን መልሶ ማልማትና እንክብካቤ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ገለጸ። የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ፓርኮች ብቸኛው በዩኔስኮ የተመዘገበ ፓርክ ነው። ፓርኩ በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ አምስት ወረዳዎች የሚዋሰን ሲሆን 412 ኪሎ ሜትር ስኩዌር የቆዳ ስፋት አለው። በዙሪያው 45 ሺህ ቤተሰቦች የሚኖሩበት ይህ ፓርክ በአደጋ ውስጥ ከሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ዝርዝር መዝገብ ውስጥ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2017 መውጣቱ ይታወሳል። እንዲያም ሆኖ በዙሪያው በሚኖሩ አርሶ አደሮች ልቅ ግጦሽ ምክንያት ፓርኩ የስጋት ጫና እንዳለበት ይነሳል። በተለይ በቅርቡ መጋቢት መጨረሻና ሚያዚያ መጀመሪያ ላይ በደረሰበት የቃጠሎ አደጋ 1 ሺህ 41 ሄክታር የሚሆነው የፓርኩ ክፍል ጉዳት እንደደረሰበት የፓርኩ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ ፓርኩን መልሶ ለማልማትና በዘላቂነት እንክብካቤ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በፓርኩ ውስጥ በርካታ ዜጎችን አሳትፎ የተካሄደው የአገር በቀል ችግኝ ተከላ ከተግባራቱ መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ''የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴው ዘላቂነት እንዲኖረው በቁጭት ርብርብ እየተደረገ ነው'' ይላሉ። እንደ አቶ አበባው ገለጻ፤ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀምም የፓርኩን ህልውና የማስቀጠል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ እንደሚሉት፤ ፓርኩን ከሰውና ከቤት እንስሳት ንኪኪ ነጻ ለማድረግም የፓርኩ የጥበቃ ሰራተኞች ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር ተቀናጅተው በመስራታቸው 80 በመቶ የሚሆነውን የፓርኩን ክፍል ነጻ ማድረግ ተችሏል። ከጀርመኑ የልማት አጋር 'አፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን' ጋር በመተባበር ለአራት ተከታታይ ዓመታት የፓርኩን ብዝሃ ህይወት፣ አስተዳደር ለማጠናከርና መሰረተ ልማት ለማልማት እየተሰራ እንደሆም አመልክተዋል። የሰሜን ጎንደር ዞን የወጣቶች አደረጃጀት አማካሪ ወጣት ጋሻው ተቀባ በበኩሉ ፓርኩን መልሶ ማልማትና እንክብካቤ ላይ ወጣቱ በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፍ አቅጣጫ ተይዞ በመሰራት ላይ እንደሆነ ይገልጻል። በፓርኩ ውስጥ ባለፈው ሀምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የተተከለውን ችግኝ ቅድመ ዝግጅት የዞኑ ወጣት አደራጀት በማስተባበር በኩል ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ለአብነትም የደሴ፣ የጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች ወጣቶች በችግኝ ተከላው ላይ እንዲሳተፉ ያደረገ ሲሆን የደባርቅ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደርና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም አሻራቸውን እንዲያሳርፉ አድርጓል። በፓርኩ ውስጥ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁም በበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በማካተት የዞኑ ወጣቶች እንክብካቤ እንዲያደርጉ የሚደረግ መሆኑን ገልጿል። ፓርኩ ካጋጠመው ችግር እንዲያገግም ችግኝ ከመትከል ባለፈ የባለቤትነት ስሜት እንዲዳብር ግንዛቤ የማስፋት እቅድ መነደፉን ነው ወጣት ጋሻው ያብራራው። በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆነው ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ከቀዳሚዎቹ ጋር የሚመደብ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም