ቀጥታ፡

ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የተሰጣቸው ቦታ የዘመናት ጥያቄያቸውን እንደመለሰላቸው የትግራይ ነዋሪዎች ተናገሩ

መቐለ ሐምሌ 19 /2011 በትግራይ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የተሰጣቸው ቦታ የዘመናት ጥያቄያቸውን እንደመለሰላቸው ነዋሪዎች ገለጹ። የክልሉ መንግሥት ለዓመታት ሲከባለል  የቆየውን  የነዋሪዎችን የመሬት ጥያቄ ለመመለስ ባደረገው ጥረት ባለፈው በጀት ዓመት ከ95 ሺህ በላይ የገጠርና የከተሞች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውቋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የቆላ ተምቤን ወረዳ የ ’ገፅኺ  ምለስለይ’’ ቀበሌ ነዋሪ  ወጣት  ስብሃት  ዘነበ  ለወጣቶች የተሰጠው  የጎጆ መውጫ ቦታ ለብዙ  ዓመታት  ሲጠበቀው  የነበረ  ነው ። ለወጣቶቹ በነብሰ ወከፍ ወጣት ከ200 እስከ 400 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ መሰጠቱንየገለጸው ወጣት ስብሃት፣ቦታው ከነበረበት ተደራራቢ ችግር እንዲላቀቅ መንገድ ከፍቶለታል። የስድስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆነ የተናገረውና በቀን ሥራ ተሰማርቶ በወር 250 ብር የቤት ኪራይ እንደሚከፍል ያስታወሰው ወጣቱ፣ ወጣቶችን ከሕገ ወጥ ስደት እንደሚታደግ እምነቱን ገልጿል። የመሬት ክፍፍሉ ነዋሪዎች የነበረባቸውን ማህበራዊ ችግሮች ከማቃለሉም ባለፈ ወጣቶች ከትውልድ ቀያቸው ሳይፈናቀሉ አምራች ኃይል እንዲሆኑ የጎላ ፋይዳ አለው ብሏል። "ወጣቶች የመሬት ተጠቃሚ በመሆናችን ለብዙ ዓመታት የተከማቸ የመልካም አስተዳደር ችግር ከመቅረፉም ባለፈ የኢኮኖሚ አቅማችንን እንዲጎለብት እየረዳን ነው" ያለው ደግሞ በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን የታሕታይ አዲያቦ ወረዳ የዓዲአውዕላ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሙለይ ግርማይ ነው ። ''የጎጆ መቀለሻ ቦታ ገዝተህ ቤት ለመገንባት በጣም ከባድ በሆነበት ወቅት መንግሥት የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንድንሆን በማመቻቸቱ ሊመሰገን ይገባል'' ብሏል። የሶስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደእሆነ የተናገረው ሌላው የራያ ዓዘቦ ወረዳ ገነት የቀበሌ ነዋሪወጣት መሰለ ሃፍተ በበኩሉ መንግሥት የጀመረው መሬትን የመስጠት ሂደት  ወጣቶች  ከስደት  ለመከላከል  አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ገልጿል። አሁን የተጀመረው የወጣቶች የመሬት ተጠቃሚነት መንግሥት አጠናክሮ እንዲቀጥልበትና  ወጣቶችም  ጥያቄዎቻቸውም በተደራጀና በትዕግስት ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም ነው ወጣት መሰለ ያሳሰበው። በአንዳንድ የመሬት ዴስክ ኃላፊዎች እየታየ ያለው የመረጃ አያያዝ ጉድለት ፣በቀጠሮ ጊዜ ማመላለስና በወጣቱ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በአግባቡ ያለመመለስ ችግሮች ሊቃለሉ ይገባል ብሏል። የክልሉ መንግሥት በቅርቡ በጀመረው የሕዝቡ ጥያቄዎችን የመመለስ ጥረት ላለፉት 20 ዓመታት ሲንከባለል የቦታ ጥያቄ እየመለሰ መሆኑ ያመለከተው ደግሞ የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ነው። በኤጀንሲው የመሬት አስተዳደር ኬዝቲም ማናጀር አቶ ገብረትንሳኤ አየለ እንዳሉት በ20111 በጀት ዓመት በክልሉ ከ95 ሺህ በላይ የገጠርና የከተሞች ወጣቶችና ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ማስገንቢያ መሬት ማግኘታቸውን አመልክተዋል። ቀደም ባለው በጀት ዓመትም በተመሳሳይ መልኩ 58 ሺህ ወጣቶችን የመሬት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ያሉት አቶ ገብረተንሳይ፣ከመካከላቸው 41በመቶ ያህሉ ሴቶች እንደነበሩ ተናግረዋል። ለዚህ ዓላማ ተብሎ ከአንድ ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ መከፋፈሉንም ገልጸዋል። አሁንም የክልሉ መንግሥት ለወጣቶች የመኖሪያ ቤት ቦታ ለመስጠት በትኩረት ይሰራል ያሉት አቶ ገብረ ትንሳኤ በ2012 በጀት ዓመትም ከ39 ሺህ በላይ  ወጣቶች  የመሬት  ተጠቃሚ  ለማድረግ  መታቀዱ  አስታውቀዋል። የክልሉ መንግሥት በከተማ የሚኖሩ 50 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  በክልሉ  ንግድ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የመሬት ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ጎይተኦም ገብረ ህይወት ናቸው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም