በአማራ ክልል ሶስት ዞኖች በአረንጓዴ አሻራ ቀን 17 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ

56
ወልድያ/ ሰቆጣ/ጎንደር ሐምሌ 19 / 2011 በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደርና ማእከላዊ ጎንደር ዞኖች ከ17 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉ ገለፀ። የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል ለኢዜአ እንዳስታወቀት በእለቱ 280 ሺህ ህዝብ በማሳተፍ 11 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ። በየወረዳው የወል የሆኑ ቦታዎች ተለይተው የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች መቆፈራቸውን ተናግረዋል ። በእለቱ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ደግሞ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገበየሁ ወርቁ ናቸው፡፡ ችግኞቹን በተፋሰሶ ስፍራዎች፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በእምነት ተቋማት፣ በመዝናኛና በትምህርት ተቋማት ለመትከል ቦታዎች ተለይተው የመትከያ ጉድጓዶች መቆፈራቸውን ገልጸዋል ። ዞኑ የተፈጥሮ ሃብት በስፋት የተመናመነበት አካባቢ በመሆኑ የአረንጓዴ ልማት ስራው አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል ። በማእከላዊ ጎንደር ዞን አራት ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኖች እንደሚተከሉ የዞኑ ግብርና መምሪያአስታውቋል። የመምሪያው ኃላፊ አቶ አንዱአለም ሙሉ እንደተናገሩት ተከላው የሚካሄደው ከ100ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ነው ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም