በደቡብ ክልል በአረንጓዴ አሻራ ቀን ከ50 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ይተከላል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል በአረንጓዴ አሻራ ቀን ከ50 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ይተከላል
ሐዋሳ ሀምሌ 19/2011 (ኢዜአ) ሐምሌ 22 / 2011 በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን በደቡብ ክልል ከ50 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸው ተገለጸ። የአረንጓዴ አሻራ ቀንን በደቡብ ክልል ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በስኬት ተግባራዊ ለማድረግ ኮማንድ ፖስት ተቋቋሞ ለተከላ የሚሆን ቦታ መረጣና የችግኝ ዝግጅቱ አጠናቅቋል ። ኮማንድ ፖስቱ ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ፣ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮዎችና ከአካባቢ ጥበቃ ደንና የአየር ንብረት ለውጥና ቁጥጥር ኤጀንሲ የተውጣጣ ነው። የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትልና የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ መና እንዳሉት በገጠርና በከተማ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ፣ ለውበት ፣ ለማገዶ፣ለግንባታ አገልግሎትና ለአካባቢ ጥበቃ ፋይዳ ያላቸው 52 ሚሊዮን 337 ሺህ 120 ችግኞች ተዘጋጅተዋል። አርሶና አርብቶ አደሮች ፣ የከተማ ነዋሪዎች ፣ ወጣቶች ፣ ሴቶችና የመንግስት ሰራተኞች በተከላው የሚሳተፉ ሲሆን፣ በ29 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጉድጓድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በገጠር በአርሶና አርብቶ አደሩ የግል ይዞታና በወል መሬት ላይ በከተማ ደግሞ በመንግስት ፣በማህበራዊና ዕምነት ተቋማት ፣ በግለሰቦች መኖሪያ አካባቢ ተከላው እንደሚከናወን ተናግረዋል። ለተከላ የተመረጠው ቦታ ነገ እንደሚደረግና የሚተከሉት ችግኞች ወደ ስፍራው ተጓጉዘው ዝግጁ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል። ችግኙ የሚተከልበት ቦታ ከሰውና እንሰሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆን የሚከለል ከመሆኑ በተጨማሪ እያንዳንዱ ችግኝ ባለቤት ተሰጥቶት የእንክብካቤ ስራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል። የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ደንና አየር ንብረት ለውጥና ቁጥጥር ኤጀንሲ ዋና ዲያሬክተር አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ በበኩላቸው በዕለቱ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ በሀገሪቱ በአረንጓዴ ልማት መስክ እየተከናወነ ያለውን ስራ መላው አለም እንዲያውቀው ያደርጋል ብለዋል። የችግኝ ተከላው የክልሉን የደን ሽፋን ወደ 25 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ሳሙኤል ተናግረዋ። ለተከላው በገጠርና በከተማ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ከባለሙያዎች ከአርሶና አርብቶ አደሩ ፣ ከወጣትና ሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በመወያየት የህዝብ ንቅናቄ መድረክ መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል። በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተሞች አረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር አቶ በጎነት ዳሌ እንዳሉት ደግሞ በሁሉም የክልሉ ከተሞች የሚገኙ አደረጃጀቶች በተከላ መርሀ ግብሩ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። በከተሞች በትምህርት ቤቶች ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፣በጤና ማእከላት ፣ በሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶችና በዕምነት ስፍራዎች የውበትና የጥላ ችግኞች ተከላ ይካሄዳል ብለዋል። እያንዳንዱ ችግኝ ባለቤት እንዲኖረው የእንክብካቤ መመሪያ መዘጋጀቱንና ከተከላ ስራው ጎን ለጎን በከተሞች የጽዳት ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል። በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት ለማድረግ ከኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት ጸጥታ የማስከበር ስራ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።