ቀጥታ፡

አቶ ገዱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተላከ መልዕክት ለግብጹ ፕሬዚዳንት አልሲሲ አደረሱ

ሀምሌ 19/2011 (ኢዜአ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  መልዕክትን ለግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ማድረሳቸው ተገለጸ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ትናንት ማምሻውን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ አቶ ገዱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተላከ መልዕክት ለፕሬዚዳንት አልሲሲ ለማድረስ ወደ ግብጽ አቅንተዋል። በአቶ ገዱ የተመራው ልዑካን ቡድን አሌክሳንደሪያ በሚገኘው ሀራምሌክ ቤተ-መንግሥት ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ወቅት ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ልዑካን ባደረገው ጉብኝት ደስታ እንደተሰማቸው መግለጻቸውን ሚኒስቴሩ አመልክቷል። የግብጽ መንግሥት ለሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ማረጋገጣቸውንም ጠቁሟል። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነው፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተላከውን መልዕክት ለፕሬዝዳንቱ አድርሰዋል፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በካይሮ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱበት ወቅት በግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር አቡበከር ሄፍኒና በካይሮ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው መሆኑን ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ አመልክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም