ሐምሌ 22 አረንጓዴ አሻራችንን ለማሳረፍ ተዘጋጅተናል - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
ሐምሌ 22 አረንጓዴ አሻራችንን ለማሳረፍ ተዘጋጅተናል - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች
ሐምሌ 19/2011 በአገር አቀፍ ደረጃ የፊታችን ሐምሌ 22 በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐግብር በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራቸውን ለማሳረፍ እንደተዘጋጁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ተቋማት ሰራተኞች ተናገሩ፡፡
በእለቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል ከታቀደው 200 ሚሊዮን ችግኝ፤ በአዲስ አበባ ከተማ 3 ሚሊዮን ለመትከል የጉድጓድ ቁፋሮና ችግኝ መዘጋጀቱን የከተማዋ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ትምህርት ቢሮ፤ የውሀና ፍሳሽ ባለስልጣንና መሬት አስተዳደር ተቋማት በእለቱ ለሚተክሉት ችግኝ የጉድጓድ ቁፋሮና ችግኝ የማዘጋጀት ስራ እያከናወኑ መሆኑን ነው የገለጹት።
የተቋማቱ ሰራተኞች በእለቱ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን ለማሳረፍ ቀኑን በጉጉት እየጠበቁ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት እንደተናገሩት፤ በቢሮው ሰራተኞች የፊታችን ሐምሌ 22 በየካ ተራራ 1ሺህ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሩ ሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች እንደሚሳተፉና ችግኙ እስኪጸድቅም ለመንከባከብ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ቢሮአቸው ክረምቱ ከገባ 5ሺ አምስት መቶ ችግኝ በመትከል አሻራውን ማሳረፍ መጀመሩና የፊታችን ሰኞም ሶስት ሺ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን የተናገሩት ደግሞ የውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ንጉስ ደሳለኝ ናቸው።
በእለቱ በድሬ ና በለገዳዲ ግድብ ላይ የአፕል ዛፎች ተከላ በተቋሙ ሰራተኞች የሚከናወን መሆኑን ያብራሩት አቶ ንጉስ፤ ችግኙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የአካባቢው አርሶአደሮች እንዲያለሙት ና እንዲጠብቁት የማስተሳሰር ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የዚሁ ተቋም ሰራተኛ አቶ ደረጄ ሰለሞን በበከሉላቸው ችግኝ አየር እንዳይዛባና የውሀ ሃብት እንዲኖር በማድረግ የሚጫወተው ሚና የላቀ በመሆኑ፤ በእለቱ አሻራቸውን ማሳረፍ ብቻ ሳይሆን የተከሉትን ችግኝ ለመንከባከብም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የፋይናንስ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን አለሙ፤ ተቋማቸው በእለቱ በየካ ተራራ 1ሺህ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ችግኝ መትከል ብቻ ውጤት የማያመጣ በመሆኑ፤ ሁሉም ሰው ችግኙን ተንከባክቦ ማጽደቅን የሁልግዜ ተግባሩ በማድረግ ሊረባረብ እንደሚገም ነው የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ሰራተኛ አቶ ንጉሴ ሰመረ የተናገሩት።
አመራሩም አቅጣጫ በመስጠትና በማስተባበር ለችግኝ ልማት ቀጣይነት መረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሰራተኛ አቶ ገብሩ ገብረኪዳን በበኩላቸው የችግኝ ተከላው መርሀ ግብር ከተማዋ ውብና ለኑሮ ተስማሚ እንድትሆን የሚጫወተው ሚና የላቀ በመሆኑ ተግባሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ ይገበዋል ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም አካባቢዎች የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙን ለማካሄድ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጀነር ታከለ ኡማ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ በታሪካዊው የአረንጓዴ አሻራ ቀን ላይ በመሳተፍ ለከተማው ያለውን ፍቅር በተግባር እንዲያሳይ ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡