ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ ኤምባሲ ሠራተኞች ችግኝ ተከሉ

ሐምሌ 18/2011 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደርና ሠራተኞች በአዲስ አበባ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የኤምባሲው ይዞታ ችግኝ ተከሉ። በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ፓቬል ማይክስ እንደተናገሩት፤ ችግኙ የተተከለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪን ተከትሎ ነው። በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት ኤምባሲው ከ50 በላይ ችግኞች መትከሉን ገልጸው ኤምባሲው ይህን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እያካሄደ ያለው የችግኝ መትከል መርሃ ግብር ይደነቃል ያሉት አምባሳደሩ የአገራቸው መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዳለው ጠቁመዋል። የአገራቸው ምጣኔ ኃብት ምንም እንኳን ኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ሲሶ ወይም አንድ ሶስተኛ የሚሆነው የአገሪቱ መሬት በአረንጓዴ መሸፈኑን ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው ክረምት አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመተከል እቅድ ተይዟል፤ እስካሁን ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተከለዋል። በመጪው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓም ደግሞ ከንጋት 12 ሠዓት እስከ ምሽት 12 ሠዓት 200 ሚሊዮን ኝግኞችን በአንድ ጀምበር ለመተከል ነው እየተሰራ ያለው። ይህም ከተሳካ እስካሁን በአንድ ቀን 65 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ደረጃውን ከያዘችው ህንድ በመላቅ፤ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ትሆናለች ተብሏል። ችግኞቹም ከአከባቢው ሥነ ምህዳር ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ የዛፍ፣ የፍራፍሬ፣ ለእንስሳት መኖ፣ እንዲሁም ለውበት የሚውሉ መሆናቸው ተጠቁሟል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም