ቀጥታ፡

ኒሳን የመኪና አምራች ድርጅት 12ሺ 500 የስራ ዘርፎችን ሊቀንስ ነው

ሐምሌ 18/2011 ግዙፉ የጃፓን መኪና አምራች ኒሳን በቅርብ ጊዜ ከገጠመው የገንዘብ ቀውስ ለማገገም  በዓለም ዙሪያ የሚገኙ 12ሺ500  ስራዎችን ሊቀንስ መሆኑ ተገልጿል። ቢቢሲ እንደዘገበው እ.ኤ.አ በመጪው 2022 መገባደጃ ላይ የማምረት አቅሙ እና የሚያመርታቸው የመኪና ሞዴሎች ብዛት ምክንያቱ ባልታወቀ መልኩ በ10 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል በመተንበዩና  ኩባንያው እ.ኤ.አ በ2019 የመጀመሪያው ሩብ አመት የተጣራ ገቢው በ94.5 በመቶ ቀንሷል። በዚህ ሩብ አመት መኪና አምራቹ ኒሳን ያስመዘገበው አፈፃፀም በአስር አመት ውስጥ ኩባንያው ካስመዘገባቸው አፈፃፀሞች አስከፊው እንደሆነ በዘገባው ተመልክቷል። የኒሳን ቁልፍ ገበያ አሜሪካ መሆኗን በመግለፅ ከሌሎች ተፎካካሪ ኩባንያዎች ጋር ያለው ትግልም እንደሚቀጥል ኩባንያው መግለፁን በመረጃው ሰፍሯል። “የሥራ ቅነሳ ለማድረግ እየሞከርን ያለው ለቁጠባ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ነው” ሲሉ  የኒሳን ዋና ኃላፊ ሄርቶ ሳካዋ መግለጫ በሰጡበት ወቅት  ተናግረዋል። የምርት ቅነሳ የሚደረግባቸው ሞደሎች የትኞቹ እንደሆነ የተገለፀ ነገር ባይኖርም፤  በኮምፓክት መኪና እና ዳትሰን ላይ ተፅዕኖ ሳያሳድር እንደማይቀር ቢቢሲ በድረ ገጹ አስነብቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም