ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም መስክ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከውጭ አገራት አቻዎቻቸው ጋር መስራት በሚችሉበት መንገድ ላይ መከሩ

ሀምሌ  18 / 2011 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም መስክ የተሰማሩ ኩባንያዎች አፍሪካን ጨምሮ ከአስር የውጭ አገራት ከመጡ አቻዎቻቸው ጋር መስራት በሚችሉበት መንገድ ላይ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ መከሩ። ''እስፖት ላይት ኦን አፍሪካ'' በሚል የተካሄደው የተናጠልና የቡድን ምክክር መድረክ  ኢትዮጵያን ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር በቱሪዝሙ ልማትና ንግድ ዘርፍ ለማስተሳሰር ብሎም በዘርፉ የውጭ አገራት ባለኃብቶችን ለመሳብ የሚያስችል ነው ተብሏል። የዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ መድረክ ሲካሄድ ይህ የኢትዮጵያው ለአራተኛ ጊዜ ነው። የቱሪዝም ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፍጹም ካሳሁን እንደሚሉት መድረኩ የኢትዮጵያ የጉዞና አስጎብኚ ድርጅቶች እንደዚሁም ሆቴሎች፤ በዘርፉ የተሰማሩ የአፍሪካና ሌሎች አገራት ኩባንያዎችን ልምድ ከመቅሰም ባሻገር በኢትዮጵያ በዘርፉ ያለውን ኃብት ለውጭ ባለኃብቶች ለማስተዋወቅ ያስችላል። የመድረኩ አስተባባሪና ተቀማጭነቱ በደቡብ አፍሪካ የሆነው የ''ሆስተን ትራቭል ማርኬቲንግ ሰርቪስ'' ባለቤት ሚስተር ዴሬክ ሆስተን በሰጡት አስተያየት የዚህ ዓይነቱ የገፅ ለገፅ  የቢዝነስ መስተጋብር ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ለቱሪዝሙ ዘርፍ መሳሪያ በሆነ ተፈጥሮ የታደለች አገር ብትሆንም ያላትን ይህንን ሃብት ወደቱሪዝም መስህብነት ቀይሮ ከመጠቀም አኳያ ብዙ እንደሚቀሯት ይነገራል። የዚህ ዓይነቱ መድረክ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። በመድረኩ ላይ ''ቨርቹዋል ሪያሊቲ ቱር'' በተሰኘው ምስለ ማሳያ ቴክኖሎጂ (ሲሙሌተር) አማካኝነት ከ360 በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ቱሪዝም መዳረሻ   በእንግዶቹ ተጎብኝቷል። አዝናኝ የሆነው ይህ ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑም ተመልክቷል። በ''እስፖት ላይት ኦን አፍሪካ'' የቢዝነስ መድረክ ላይ ከተሳተፉት አገራት መካከል ኬንያ፣  ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ሲሼልስ ይገኙበታል። በመድረኩ ላይ የየአገራቱ ሆቴሎች፣ የአስጎብኚ ድርጅቶ፣ የጉዞ ወኪሎችና የአየር መንገድ አገልግሎት ሰጪዎች ተገኝተዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም