የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በችግኝ ተከላ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በችግኝ ተከላ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናቸው
ሀምሌ 18 / 2011 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙኃን ህብረተሰቡን ከመቀስቀስ ባሻገር በተግባር ችግኝ በመትከል አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የሚዲያ ተቋማት ከመደበኛ የዘገባ ሽፋናቸው ባሻገር በችግኝ ተከላ ዘመቻው ተግባራዊ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። የአሀዱ 94 ነጥብ 3 ሬዲዮ ጣቢያ 'ቤተሰቦቸ' ለሚላቸው አድማጮቹ በመጪው እሁድ ሀምሌ 21 ቀን 2011 ዓ.ም 'በጋራ ችግኝ እንትከል' ጥሪ ማቅረቡን የጣቢያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ ገልፀዋል። አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች የደን ሃብታቸው በተሻለ ደረጃ እንደሚገኝ የገለጹት ስራ አስኪያጁ፣ ኢትዮጵያ ግን በሰው ሰራሽ መንስኤዎች የደን ሃብቷ በከፍተኛ ሁኔታ በመመናመኑ ለድርቅና ለረሃብ ተጋላጭ መሆኗን አስረድተዋል። በደን ልማት በኩል የቀድሞው መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደነበራቸውና በደን ሽፋን ላይ መልካም አሻራ ማሳረፋቸውን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ሲገባ በ2000 ዓ.ም የዛፍ ችግኝ ለመትከል እንቅስቃሴ ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል። አገራዊ እይታ ባላቸው መርሃ ግብሮች መገናኛ ብዙሃን መደገፍና ማስተባበር እንደሚገባቸው ገልጸው፤ ለአብነትም በዘንድሮው የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም ተቋማቱ መሳተፍ፣ መደገፍና ማስተባበር እንዳለባቸው ገልጸዋል። ሬዲዮ ጣቢያው 'ለቡ' በተባለው አካባቢ በተሰጠው የአንድ ሺህ ጉድጓዶች ከአድማጮቹ ጋር በጋራ ለመትክል ባቀረበው ጥሪ መሰረት የሰዎች ፈቃደኝነት ምላሽ ከተጠበቀው በላይ እንደሆነ አብራርተዋል። ይህ በትንሽ ማስታወቂያ የተገኘው ምላሽ ወደፊት ሰፊ የደን ልማት ፕሮጀክት በመንደፍ ሰፊ ስራ መስራትና አገራዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል መነሻ ሆኗል ነው ያሉት። የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች በጋራ በመሆን በየዓመቱ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በመሳተፍ በደን ሽፋን ላይ ትልቅ አገራዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ድርጅታቸውም ወደፊት በየዓመቱ በችግኝ ተከላ መርሃግብር እንደሚሳተፍ፣ በተተከሉ ችግኞች ፅድቀትና እንክብካቤ ላይ ህብረተሰቡን በማነቃቃት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አቶ ጥበቡ አረጋግጠዋል። የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ደረጀ በበኩላቸው ድርጅቱ በችግኝ ተከላ ህብረተሰቡን ከመቀስቀስና ሰፊ ሽፋን ከመስጠት ባለፈ በችግኝ ተከላ ተግባር ተሳትፎ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ድርጅቱ ለችግኝ መትከያ ቦታ ስላልተሰጠው በተቋሙ ግቢ ውስጥ ሰራተኞችን በማሳተፍ 300 ችግኞችን ሐምሌ 22 ቀን 2011 በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ቀን ላይ አስተዋጽኦውን እንደሚያበረክት ተናግረዋል። ችግኝ መትከል አገራዊ የዜግነት ግዴታ መሆኑን ገልጸው መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው ህብረተሰቡን ከመቀስቀስ ባሻገር በተግባር መሳተፍ እንዳለባቸው አብራርተዋል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታደሰ ድርጅቱ 78ኛ የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ከነዚህም መካከል ከዚህ በፊት በመዲናዋ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ የድርጅቱ ሰራተኞች በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መሳተፋቸውን ገልጸዋል። በመጪው ሰኞ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው የ200 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ ዘመቻ ከአንድ ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።