ሕያው ልሳን

29
አየለ ያረጋል-ኢዜአ ሊቃውንተ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምቷ አገራቸው ከትከሻዋ ሸማ፣ ከእጇ ዶማ፣ ከጣቷ መቃ ፣ ከአንደበቷ ዜማ ጠፍቶ እንደማያውቅ ያትታሉ። ቆፍሮ፣ አርሶ፣ ዘርቶ፣ አምርቶ የብዙ ሲሳይ ባለቤት እንደነበረች ጥንተ ታሪኳን ያነሳሉ። ዲያቆን መርሻ አለኸኝ (ዶክተር) "እንደ ልብ የመቃምና የመጉረስ፣ ወርቅና ብርን አቅልጦ የማጌጥን፣ ብረትን ቀጥቅጦና አቅልጦ መሳሪያ የማንገት ፍልስፍና ነበራት" በማለት ስነ ስዕል፣ ቅርጻ ቅርጾች፣ ሐውልቶች፣ ባህላዊ ክውን ጥበባቷን በ 'ንቡርነት' ይጠቅሳሉ። የዕውቀት ጥማቷ፣ የመፍጠር ክሂሏ፣ የተቃና ለጆሮ የማይጎረብጥ 'ፊደል' ቀርጻ ዓለምን ያስቀና የታሪክ፣ የትምህርት፣ የፍልስፍና፣ የሂሳብ፣ የቁጥር ሥሌት ወዘተ… ጥበባት ጽፋለች። በእልፍ ዘመናት አዙሪት በድንጋይ፣ በሸክላ፣ በሐውልት፣ በብራና ሰሌዳዎች ማንነቷን ከትባለች። ይሄም በምድራችን ከጥንት ጀምሮ ፊደል ከነበራቸው እንደ ቆስጠንጥንያ፣ግብጽ፣ሩስያ፣ዕብራዊያንና መሰል ዕፍኝ የማይሞሉ አገሮች አንዷ አድርጓታል። በቀመረችው ፊደል ስርዓተ ጽሕፈት በመፍጠሯም የፊደል፣ ቁጥርና ስነ ጽሁፍ ሀብት ባለጸጋ ሆናለች።ለእነዚህ ክታቦቿ መሰረት ታዲያ የ'ግእዝ ቋንቋ' ነው። ፊደል ትዕምርተ ድምጽ ነው-የድምጽ ወኪል። እነ ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ (ዘብሔረ ቡልጋ) 'ፊደል ምሁራን መጋቢ' እያሉ ተቀኝተዋል። የግእዝና የአቡሻክር ሊቁ አለቃ አስረስ የኔሰው (ዘብሔረ ጎጃም) "ቋንቋ መልክ ነው፤ መልክም ቋንቋ ነው፤ፊደል ሐውልት ነው፤ ሐውልትም ፊደል ነው፤ ፊደል መልክ ነው፤ መልክም ፊደል ነው" ይላሉ። "ፊደል ዓላማ ነው፤ ዓላማም ፊደል ነው፤ ዓላማ የኩራት ምልክት ነው፤ ኩራትም ነጻነት ነው" ሲሉ ያመሰጥራሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳንና ስነ ጽሁፍ መምህሩ አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ደግሞ "ፊደል የድምጽ ወኪል ብቻ አይደለም፤ ሙዳየ ምስጢራት ነው፤ የመልዕክት ማከማቻ ስልቻ ነው፤ ፊደል ቅርስ ነው" ይሉታል። በፊደል ቅርስነት የሚስማሙት የሥነ ልሳን ሊቁ ባዬ ይማም (ፕሮፈሰር) 'የፊደል ቅርሳችን ሐውልት ሊቆምለት ይገባል' የሚል እሳቤ ያራምዳሉ። ‘በእጅ የያዙት ወርቅ…’ ሆኖ እንጂ ነገሩ ‘የኢትዮጵያ ፊደል’ ከሰው ዘር መገኛነቷ፣ ከግብርና ተላሚነቷ ባልተናነሰ የስልጣኔዋ መገለጫ ‘ዘላለማዊ ሀብቷ’ ተደርጎ መወሰድ እንደሚገባው ሊቃውንቱ ይሞግታሉ። በአለቃ አስረስ የኔሰው ትንታኔ የግእዝ ፊደላት የራሳቸው ትዕምርት፣ ቁጥርና ትርጓሜ አላቸው። የፊደሉ ባለቤት ደግሞ 'ግእዝ ቋንቋ' ነው። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካም የፊደል ባለቤት፣ ጥንታዊና የሥነ ፅሁፍ ሀብቶች የከበረ ቋንቋ አለመኖሩ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። በግዕዝ ቋንቋ ላይ አያሌ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሊቃውንት ብዙ ብለዋል፤ እያሉም ነው። በቋንቋው የትመጣ (origin) ሁሉን ሊቃውንት የሚያስማማ ጥናት የለም። ነገር ግን በቋንቋው 'ጥንታዊነት' ሁሉም ተመራማሪዎች ይስማማሉ። ግእዝ ሁሉንም የዓለም ቋንቋዎች የመግለጽ አቅም እንዳለው ብዙዎቹ ይናገራሉ። ጀርመናዊው የልሳነ ግእዝ ተመራማሪ ኦገስት ዲልማን “የግእዝ ቀንቋ ሥነ ጽሁፍ ሁሉንም አርዕስት የዳሰሰ በመሆኑ ከኢትዮጵያዊያን አልፎ በአውሮፓዊያን የተፈለገ ልሳን ነው“ ብለውታል። በዲልማን ሃሳብ የሚስማሙት ዶክተር መርሻ ግእዝ ከጥንት አክሱማውያን ጀምሮ ለአያሌ ዓመታት ከሐይማኖት ልሳንነት ባሻገር ለመግባቢያ፣ አፍ መፍቻነትና ልሳነ ነገስታት ሆኖ ያገለገለ ብሔራዊ የሥነ ጽሁፍ ቋንቋ እንደነበር ያትታሉ። ከሶስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሐውልት ላይ ሲጻፍ እንደነበር የሚገልጹት ሊቀ ኅሩያን ተግባሩ አዳነ ደግሞ ‘ኢትዮጵያ ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምራ ዓርባዕቱን ወንጌልና ምልክት አልባውን የቅዱስ ያሬድ ድጓ ጻፈች። ከሸንበቆ ብዕር (መቃ) ቀርጸው፣ ከዕጽዋት ቀለም በጥብጠው፣ ከእንስሳት ቆዳ ብራና ዳምጠው ታሪክ፣ ባህል፣ መድሃኒት፣ ስነ ክዋከብት፣ ስዕል፣ የዘመን ቀመርና አቡሻክር፣ ዜማ (ሙዚቃ) መጻሕፍትን ጽፈዋል” ይላሉ። አያሌ ሊቃውንትም የግእዝ ጽሁፎች ከቀይ ባህር እስከ ሳዑዲ አረቢያ ባህረ ገብ፤ ከቤተ ክህነት እስከ ቤተ መንግስት፣ ከቅኔ እስከ ዜማ፣ ከፍልስፍና እስከ ሥነ ክዋክብት፣ ከጥንት እስከ ዘመነኛ ታሪክ፣ ከምስጢር መክፈቻ እስከ ሃሳብ መስጫ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፖለቲካዊ፣ ማኅበረሰባዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳይ ያቀፈ ልሳን እንደሆነ ያስረዳሉ። ታሪክ፣ መድሃኒት፣ ቅኔ፣ ዜማ፣ ፍልስፍና፣ ስነ ክዋክብት፣ የቁጥር ስሌት፣ ሥነ ስዕል፣ ሥነ ምግባር፣ ሕግና ሥነ መለኮት አገር በቀል ዕውቀቶች ተሰንደውበታል። ከ14ኛው እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን 'ዜና መዋዕሎች' በስፋት ተጽፈውበታል። ለአብነትም ዛሬ ላይ በጥንታዊ ሥነ ጽሁፍ ሀብትነት የሚጠቀሱት ጥንታዊ ገድላት፣ ድርሳናት፣ ሃዲሳት፣ ብሉያት፣ ቅዳሴያት፣ ታምራት፣ ፍትሐ ነገስት፣ ክብረ ነገስት፣ አቡሻክር፣ አንገረ ፈላስፋ፣ መጽሐፈ ጠቢባን በዚህ ጊዜ ውስጥ በግዕዝ ቋንቋ ተጽፈው ነበር። ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ካስመዘገበቻቸው 12 የሥነ ጽሁፍ ሀብቶች መካከል አብዛኛዎቹ በግዕዝ ቋንቋ ብራና ላይ የተከተቡ ናቸው። (አርባዕቱ ወንጌላዊያን፤ የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክታት፣ ግብረ ህማማት፣ መዝሙረ ዳዊት (ለሕትመት የበቃ የመጀመሪያው መጽሐፍ) ይጠቀሳሉ)። ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም፡- … ከአዳም ከኖኅ ከእናት አባቷ ለሴም የታጨች ከነ ውበቷ ከንጉሡም ከእግዚሄር ከባለቤቷ ስለተሰጠች እቴጌነቷ እንዲህ ብታዩዋት ደሃ መስላችሁ ባለጸጋ ናት ግእዝ ቋንቋችሁ... በማለት የግእዝን ታላቅነት ተቀኝተዋል። ግእዝ ቋንቋ በተለይም ከአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እየተዳከመ እንደመጣ ታሪክ ያስረዳል። ዛሬ ላይ በቋንቋው አፍ የሚፈታበት የህብረተሰብ ክፍል የለም። የቤተ ክርስቲያን የምስጋናና የጸሎት ማቅረቢያ ነው። በዩኒቨርሲቲዎችም የምርምር ቋንቋ ነው። እስካሁን ተጠብቆ በቆየባት ቤተ ክርስቲያንም ግእዝ እጅግ መዳከሙ ይነገራል። በዚህም ‘ግእዝ ያለፈበት ነው፤ የሞተ ቋንቋ ነው’ የሚሉ በርካታ ወገኖች አሉ። ይሁንና ሌሎች አያሌ ሊቃውንት ልሳነ ግእዝ አልሞተም በማለት ይሞግታሉ። በሥነ ልሳን ተመራማሪዎች ጽንሰ ሃሳብ አንድ ቋንቋ ሞተ ለማለት ሁለት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው ቋንቋው ወግና ማንነቱን በሌላ ሲተካ፣ በሌላ እየተዋጠ ራሱን ሲያጣ ወይም ራሱን ሲገድል ነው። ሁለተኛው ደግሞ ቋንቋው በሌላ ቤተሰብ ቋንቋ ሲገደል ወይም በአንድ ማህበረሰብ በተመሳሳይ ወቅት በሚያገለግሉበት ጊዜ አንዱ በአንዱ ሲዋጥ ነው። ይህም ከአንድ ቤተሰብ የማይመደቡ ሁለት ቋንቋዎች በሚያደረጉት ውህደት የሚፈጠር ነው። በሌላ በኩል ቋንቋው በአፍ መፍቻነት የሚገለገልበት ሲጠፋና የሚያስረዳና ቋንቋውን የሚያስተምር ሲጠፋ ነው። በሶስት ጽንሰ ሃሳቦች ሲተነተን ግን 'ግእዝ ሙታን ልሳን ነው' ለማለት አያስደፍርም። ለምሳሌ በመጀመሪያው ጽንሰ ሃሳብ ግእዝ በሌላ ቋንቋ አልተዋጠም። (ለምሳሌ በአማርኛ ቋንቋ 33 ፊደላት ውስጥ 27 የግዕዝ ናቸው። አማርኛ ከግእዝ ቃላትና ሰዋሰውን ወረሰ እንጂ ግእዝ በአማርኛ አልተዋጠም በማለት ይከራከራሉ)። በሁለተኛውም መስፈርትም ግዕዝ በየትኛውም አገራዊም ሆነ ባዕድ ቋንቋ አልተገደለም። (ለምሳሌ ተፅዕኖ አድርገውበታል ከሚባሉት የአማርኛ ወይም ትግርኛ ቋንቋዎች ውህደት ማንነቱን አጣ ለማለት አያስችልም። 'ምክንያቱም ሁሉም የአንድ ቤተሰብ (ሴማዊ) እንጂ ሌላ ወገን አይደሉምና' ሲሉ ይሞግታሉ)። ምናልባት በመጨረሻው ትንታኔ ግእዝ በአፍ መፍቻነት የሚጠቀምበት አለመኖሩ 'ሞቷል' ሊያሰኝ ይችላል። ነገር ግን በአፍ መፍቻነት ባያገለግልም እንኳን ዛሬም ድረስ አያሌ ሊቃውንት የሚወጡበትና በየገዳማትና አድባራቱ ትምህርቱ በየደረጃው የሚሰጥበት፤ አንዳንድ መጽሐፍት ዛሬም ድረስ ጽሁፍ የሚደርሱበት ቋንቋ ነው በማለት 'ግእዝ አልሞተም' የሚሉ ወገኖች ይከራከራሉ። ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን "ግእዝ አይሞትም፤ ሕያው ልሳን” ነው በማለት በ'ትንሳኤ ግእዝ' መጽሐፋቸው አስፍረዋል። ሊቃውንቱም ግእዝ ለአማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጉራጊኛና ሌሎች የሴም ቋንቋ ንዑስ ቤተሰቦች ስነ ጽሁፍ እንደ ጨው የሚያገለግል ቅመም እነደሆነ በመግለጽ ያሞካሹታል። በርግጥ ግእዝ ከኢትዮጵያ አልፎ ሌሎች አገሮችም እያስተማሩትና እየተመራመሩበት መሆኑ እሙን ነው። በዚህ ቁጭትም ይመስላል ዛሬ ላይ ግእዝ መልሶ እንዲያንሰራራ የሚጎተጉቱ ግለሰቦችና ተቋማት የተበራከቱት። በርካታ መዝገበ ቃላትና የግእዝ መማሪያ መጻሕፍት እየተጻፉ ነው። ከሰሞኑ ለአራተኛ ጊዜ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው 'የግእዝ አገር አቀፍ ጉባኤ'ም ከዚህ የመነጨ ነው። በጉባኤው በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡበትና የወደፊት ይሁንታዎች የተጠቀሱበት ነበር። በጉባኤው ላይ "ግእዝና ኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ ጥናታቸውን ያቀረቡት መምህር ዘርዓዳዊት አድሃና፤ "ኢትዮጵያ ሲባል ህዝቦቿ ናቸው፤ እነዚህ ህዝቦች ደግሞ በዚህ ቋንቋ የጋራ ታሪካቸውን አስፍረዋል፣ ለብዙ ሺ ዘመናት ተግባብተውበታል፣ ጽፈውበታል፣ አዚመውበታል፣ በጥቅሉ አገር ገንብተውበታል" ይላሉ። "ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎቻችን ቀድሞ መጻፊያ፣ ማዜሚያ፣ መድረሻ የነበረው የግእዝ ቋንቋ  ነበር" ያሉት አጥኚው፤ ቋንቋው ለተሰወነ ህዝብና ሃይማኖት ብቻ ተደርጎ መወሰድ የሌለበት ልሳን እንደሆነ ያብራራሉ። የግእዝ ቁጥሮች ከዓለም የተለዩና በፊደል ደረጃ የተቀረጹ በመሆኑ ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚከሰተው የገንዘብ ደህንነት ችግር (ማጭበርበር) ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነም ሊቃውንቱ ያብራራሉ። ለምሳሌ፡- በገንዘብ መክፈያ ሰነድ (ቼክ) ላይ የሚደርሰውን ማጭበርበር (በአረብኛ ቁጥሮች) ለመከላከል በፊደል ይጻፋል። ነገር ግን በግእዙ ቁጥሮቹ አንዱ ወደ አንዱ የማይቀየሩ ስለሆነ በፊደል መጻፍና ብዙ አሃዞችን ማስቀመጥ አያስፈልግም። እናም ለገንዘብ ደህንነት የግእዝ ቁጥሮች ሌላው ዓለም ቢጠቀምባቸው መልካም እንደሆነ ያመላክታሉ። የአገር በቀል ዕውቀቶች ልማታዊ ፋይዳ፣ የግዕዝ ፊደላትና ፍካሬ ከዋክብት፣ የግእዝ ቁጥሮች፣ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ ክዋኔ ጥበባት ለአገራችን ትያትር ዕድገት ያለው ግብዓት፣ የግእዝ ቋንቋ ጥናት ትውፊቱና ትንቢቱ በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡ ጥናቶች መካከል ነበሩ። የጥናቶቹ ይሁንታም 'የግእዝ ቋንቋ የያዛቸውን ዕውቀቶች ለመጠቀምና ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ቋንቋውን በስርዓተ ትምህርት አካቶ ማስተማር ይገባል' የሚሉ ናቸው። ዛሬ ላይ ቋንቋውን የውስን ሕብረተሰብና ኃይማኖት ብቻ አድርጎ የማየትና ቸልተኛ መሆን ምክንያቶች ግእዝ በብዙ መልኩ መዳከሙን አንስተው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ቋንቋውን አሳድጋ ለዘመናት የተጠቀመችበት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት መሆኑን አስገንዝበዋል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ የአገረሰብ ዕውቀቶች ጥናት ተቋም ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ አዲሱ ዘገየ 'የአገር በቀል ዕውቀቶችና ልማታዊ ፋይዳዎች' በሚል ባቀረቡት ጥናት፤ አገር በቀል ዕውቀቶች በህክምና፣ በተፈጥሮ ጥበቃ፣ በግብርና ስራ ዘዴ፣ በአገረሰባዊ ቴክኖሎጂዎች ወይም ዕደ ጥበባት፣ የማይዳሰሱ ርዕዮተ ዓለማትና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ዕውቀቶች በግእዝ መጽሐፍትና ድርሳናት እንደሚገኙ ይገልጻሉ። ስለሆነም በቋንቋው የተደረሱ እነዚህን ዕምቅ አገረሰባዊ ዕውቀቶችና ጽንሰ ሃሳቦች ለአገር ልማት ማዋልና ይበልጥ መመራመር፣ በቁጭት መቆፈር እንደሚገባ ነው የተናገሩት። አቶ ይኩኖአመላክ 'በቋንቋው የተጻፉ ዕውቀቶችን ለዘመናዊ ትምህርቶች ግብዓት መጠቀምና ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል' ይላሉ። ቋንቋው የያዛቸውን አገር በቀል ዕውቀቶችና ጥበባት ለመጠቀም በስርዓተ ትምህርቱ ማካተትና በንባብ ስልት መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቅዱስ ያሬድ ጥንታዊ ስነ ጽሁፍና ብራና ጥናቶች ማዕከል መምህሩ ዶክተር ሐጎስ አብርሃ "ገና ምዕራባዊያን ሳይጀምሩት ኢትዮጵያ ፍካሬ ከዋክብት ባለቤት እንደነበረች በጥናት ተረጋግጧል" ይላሉ። በጉራጌ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ መልከ ጸዴቅ ግእዝን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብቻ አድርጎ መቁጠር እንደማይገባ ይገልጻሉ። በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በግዕዝ የተጻፉ ጥንታዊ መጽሐፍት ከኃይማኖታዊ ይዘታቸው ባለፈ ስነ ጽሁፋዊ፣ ታሪካዊና ማህበራዊ ጥናት የሚተነተንባቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። ቤተ ክርስቲያኗ እስካሁን ጠብቃ በማቆየቷና ዘመናዊ ትምህርት ሳይገባ የራሷ ስርዓተ ትምህርት ቀርጻ መሀይምነትን ስትዋጋ መቆየቷ የሚያስመሰግናት ተግባር እንደሆነም ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሱ በፈረንሳይ፣ በሮማና በጀርመን በተዘዋወሩባቸው ከተሞች ግእዝ ትምህርት እንደሚሰጥ ማረጋገጣቸውን ገልጸው፤  የግእዝ ምስጢሩን ባዕዳን ሳይቀር ለመፈልቀቅ እየጣሩ የቋንቋው ባለቤቶች ቸልተኛ መሆን እንደሚቆጫቸው ይገልጻሉ። ምሁራኑ ቋንቋው ሁሉንም ጉዳይ ያቀፈ በመሆኑ በስነ ልሳን፣ በታሪክ፣ በስነ ሰብዕ፣ በስነ ጽሁፍ ጥናትና ምርምር ሊደረግበት እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ግዐዝ ለአገሪቱ የኩራትና የማንነት መገለጫ ነው፤ ራሷን፣ ዕውቀቷን፣ ትምህርቷን ታሪኳን ጽፋለችና ቅርሷ ነውና መታወቅና መመርመር አለበት። ቤተ ክህነት ትውልዱን የዋጀ ሳይንሳዊ ስርዓተ ትምህርት መቅረጽ አለባት፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቋንቋው ይሰጥ፤ የራሱ የቋንቋ ትምህርት ክፍል ይከፈትለት፣ የግእዝ ዐውደ ጥናቶች ይካሄዱ፣ ብሮሸሮች ይታተሙ፣ በቴክኖሊጂ ታግዞ ትምህርቱን መስጠትና ከሰዋሰው ይልቅ የንባብ ስልተ ትምህርት (Pedagogy) አሰራር መከተል ያስፈልጋል። አማርኛ ሳይቀር ልጆቻቸውን የነፈጉ ወላጆች ልጆቻቸውን ግዕዝ ያስተምሩ፤ ጥናትና ምርምር ተቋማት ይቋቋሙና ግዕዝን በሚገባው ደረጃ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ግዕዝ በአፍ መፍቻ ቋንቋነት ባያገለግልም የአገሪቱ ሁለንተናዊ ገጽታ የተገለጸበትና ይዞ የሚገኝ በመሆኑ ዛሬም ወደፊትም 'ሕያው ልሳን' ነው። በሌላ በኩል ቋንቋው አፍሪካን ወክሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በባሕል ቅርስነት መወከል የሚችልና የሚያስፈልገው ነው፤ ለዚህም ሕጋዊ ጥበቃ የሚያስፈልገው ሀብት ነው የሚሉም አልጠፉ። በአገር ውስጥ ያሉ በርካታ ቋንቋዎችም ከላቲን ወደ ግእዝ ፊደላት ቢጠቀሙ ተመራጭና አገራዊ ትርፉ የትየሌሌ እንደሆነም ይናገራሉ። በመጨረሻም አለቃ አስረስ ከአምሳ ዓመት በፊት 'የካም መታሰቢያ' በሚል መጽሐፋቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት እንሰናበት። “የኢትዮጵያ ልጆች ተጠንቀቁ፤ የግእዝን መጽሐፍት አትናቁ፤ በግዕዝ መጽሐፍት ውስጥ ብዙ ጥቅም ለማግኘት ትችላላችሁ። ጥንታዊ የማዕድን ቦታዎችንና የአገራችሁን የክብር መዝገብ ለማግኘት ትችላላችሁ። የውጭ አገር ሰዎች ጥንታዊውን መጻሕፍትት በውድ ዋጋ ሊገዙ ለምን የፈለጉ ይመስላችኋል? የውጭ አገር ሰዎች ለፖለቲካ የጻፉትን ለመቀበል ያደረሰን የግእዝን መጻሕፍት በሰፊው ካለመመርመር የተነሳ ነው።"                                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም