የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች በ'አረንጓዴ አሻራ ቀን' 15 ሺህ ችግኝ ለመትከል ዝግጅቱን አጠናቋል

  አዲስ  አበባ   ሀምሌ 18/2011የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች በ'አረንጓዴ አሻራ ቀን' 15 ሺህ ችግኝ ለመትከል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገለጸ። ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በዘንድሮው የክረምት ወቅት እየተካሄደ ባለው የዛፍ ችግኝ ተከላ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። የሚኒስቴሩ አመራርና ሰራተኞች ሐምሌ 22 ቀን 2011ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 'በአረንጓዴ አሻራ ቀን አሻራችንን እናኑር!' በሚል መሪ ቃል በኦሮሚያ ክልል ሎሜ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ከ15 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አስታውቋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የ'አረንጓዴ አሻራ ቀን' በሚል መሪ ቃል በተያዘው የ200 ሚሊየን ችግኝ በአንድ ጀምበር እቅድ መሰረት የችግኝ ተከላ የሚያከናውነው ሚኒስቴሩ፤ የሚተከሉ ችግኞችን በዘላቂነት ለመንከባከብ በሎሜ ወረዳ የተጎዱ መሬቶች ማገገሚያ ፕሮጄክትና በአካባቢው ሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች ጋር ከመግባባት ላይ መድረሱን ገልጿል። ሚኒስቴሩ የሰላም የህጻናት መንደር ሰራተኞችን በማስተባበር እንዲሁም በሁለቱም አካባቢዎች ለተተከሉ ችግኞች ዘላቂ ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎችንና አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ችግኞችን እንደሚንከባከብ አስታውቋል። የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች ሰኔ 9 ቀን የአፍሪካ ህጻናት ቀን በዓል ጋር በማስተሳሰር በሰላም የህጻናት መንደር ከአንድ ሺህ በላይ ችግኞች መትከላቸው ያስታወሰው መግለጫው፤ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለማስጀመር በአዳማ ከተማ ከተዘጋጀው መርሃ ግብር ጋር በማያያዝም ከአራት ሺህ በላይ ችግኞች መተከሉን ገልጿል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም