ቀጥታ፡

ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ምርት ሊያቆም መሆኑን አስታወቀ

ሐምሌ 18/2011 የአሜሪካው የአውሮፕላን አምራች ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ምርት በጊዜያዊነት ሊያቆም መሆኑን ገለጸ። ቦይንግ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም ባለው የሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደገጠመው ትናንት ይፋ አድርጓል። ኩባንያው በታሪኩ በሶስት ወራት ውስጥ ያገጠመው ትልቁ ኪሳራ ነውም ተብሏል። ከበረራ የታገዱት የ737 ማክስ አውሮፕላኖች ወደ በረራ የሚመለሱበት ጊዜ የሚዘገይ ከሆነ አውሮፕላኖችን ማምረት እንደሚያቆም ነው ኩባንያው የገለጸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሲቪል አቪዬሽን ተቆጣጣሪዎች ጋር የሚደረገው ክርክርና ችግር የሚቀጥል ከሆነ ቦይንግ የ737 ማክስ አውሮፕላኖችን ምርት መቀነስ አለበለዚያዘም በጊዜያዊነት ላልተወሰነ ጊዜ አውሮፕላኖቹን ማምረት እንደሚያቆም የኩባንያው ሃላፊ ዴኒስ ሙለንበርግ ተናግረዋል። ያም ቢሆን አውሮፕላኖቹ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም ወደ በረራ ይመለሳል ብለው እንደሚያምኑም አመልክተዋል። "የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በደህንነት ወደ በረራ እንዲመለሱ የምናደርገው ድጋፍ ይቀጥላል፤ የአውሮፕላኖቹ የማምረት እቅድ ላይ ግምገማ ይደረጋል" ብለዋል ዴኒስ ሙለንበርግ ከባለሀብቶች ጋር በነበራቸው ውይይት። መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተከስክክሶ የ157 ተሳፋሪዎች ህይወት ካለፈ በኋላ አውሮፕላኑ በመላው ዓለም በረራ እንዳያደርግ እገዳ እንደተጣለበት ይታወሳል። ከአምስት ወር በፊትም የኢንዶኔዢያው 737 ማክስ አውሮፕላን ተከስክሶ የ181 ተሳፋሪዎች ህይወትም እንዳለፈም የሚታወቅ ነው። "ኩባንያው የ737 ማክስ አውሮፕላኖች ይመለሱበታል ብሎ ካስቀመጠው ጊዜ ላይ ለውጥ የሚኖር ከሆነ የአውሮፕላኖች ምርት የመቀነስ ወይም  የማክስ ምርቶችን በጊዜያዊነት ማምረት ማቆምን ጨምሮ ሌሎች አማራጮች ይወስዳል" ብለዋል የኩባንያው ሃላፊ። ለሁለቱ አውሮፕላኖች መከስከስ ምክንያት ዝርዝር ምርመራ እየተካሄደ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች እንዲሁም የአየር በረራ ደህንነት ባለስልጣናት አውሮፕላኖቹ ኤምካስ ተብሎ የሚጠራው መተግበሪያቸው ላይ እክል መኖሩን ጠቁመዋል። ቦይንግ በኤምካስ ስርዓቱ ላይ ችግር እንዳለ በማመን ችግሩን ለማስተካከል እየሰራ ይገኛል። በ150 አገራት ደምበኞች ያሉት የቦይንግ ኩባንያ ከዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ተቆጣጣሪዎች የበረራው እገዳ ተነስቶለት ወደ በረራ መመለስ የሚያስችለውን ፈቃድ ተቆጣጣሪዎች ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል። የቦይንግ ኩባንያ ሃላፊ ዴኒስ ሙለንበርግ ኩባንያው በየሳምንቱ ከ737 ማከስ አውሮፕላን ባለሙያዎች ጋር የቴክኒክ ስብሰባዎችን እያካሄደ መሆኑንና በተሻሻለው መተግበሪያም እስካሁን 225 ምስለ በረራ እንዳካሄደም ገልጸዋል። ከምንም ከማንም በላይ በአሁኑ ሰአት በአውሮፕላን አደጋው ተጎጂ የሆኑ ቤተሰቦችና ወዳጆቻችው የፈተና ወቅት እንደሆነም ጠቅሰዋል። በተጨማሪም በዓለም ደረጃ ተሳፋሪዎችን የማስተሳሰርና የመጠበቅ ዋንኛ ትኩረታቸውን ጥራትና ደህንነት ላይ ትኩረት አድርገው የኩባንያው ራዕይ ለማሳካት በከፍተኛ የስራ ስነ ምግባር ያለማቋረጥ በትጋት እያከናወኑ ላሉትም የኩባንያው ሰራተኞች የፈተና ጊዜም እንደሆነም ገልጸዋል። "አሁን ያለው ጊዜ ለቦይንግ ወሳኝ የሚባለው ወቅት ነው በጋራ በመሆን የፈተና ጊዜውን በጥንካሬ በማለፍ የተሻለ ስራ ለመስራት ኩባንያው ቁርጠኛ ነው" ብለዋል ሃላፊው። ከሁለቱ የአውሮፕላን አደጋዎች በኋላ በወር የሚመረተው የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርቶች ቁጥር ከ52 ወደ 42 መቀነሱንም አመልክተዋል። ኩባንያው የሚያመርተው ምርት በመቀነሱ ምክንያት፤ ለአውሮፕላኑ ምርት ለሚያስፈልጉ ግብአቶች የሚያወጣው ወጪ መጨመሩንም ነው የቢቢሲ ዘገባ የሚያመለክተው። የማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ በመታገዳቸው ለተለያዩ አየር መንገዶች ሊያቀርባቸው የነበሩ አውሮፕላኖቹንም ላልተወሰነ ጊዜ በማገዱ በዚህም ምከንያት ገቢ መሰብሰብ ባለመቻሉ የኩባንያው የገንዘብ ፍሰትና ትርፍ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩም እየተገለጸ ይገኛል። የአሜሪካ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከመተግበሪያ ችግሩ በተጨማሪ አውሮፕላኑ ሌላ እንከን እንዳለበት በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም መግለጹ ይታወሳል። አስተዳደሩ አውሮፕላኑን ላይ ተጨማሪ እንከን እንዳለ ያረጋገጠው በአውሮፕላኑ ላይ በተደረገው የምስለ በረራ ሙከራ እንደሆነ ቢገልጽም በእንከኑ ዙሪያ ዝርዝር ማብሪሪያ ከመስጠት መቆጠቡ ይታወቃል። የአሜሪካ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ይሄን ማለቱ ተከትሎ ኩባንያው በያዝነው ወር ሊያደርገው የነበረውን የአውሮፕላኑ የሙከራ በረራ እንዳዘገየውም አይዘነጋም። የቦይንግ ኩባንያ ለመጨረሻ ጊዜ የአውሮፕላን ምርቱን አቁሞ የነበረው የኮሪያ አየር መንገድ ንብረት የነበረው የቦይንግ 747-3B5B አውሮፕላን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1997 ከደቡብ ኮሪያ ተነስቶ የአሜሪካ የፓሲፊክ ግዛት በሆነችው ጉዋም በሚገኘው አየር ማረፊያ 5 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ቦታ ተከስክሶ ከደረሰው አደጋ በኋላ ነው። በአደጋው በአውሮፕላኑ ተሳፍረው ከነበሩ 254 ሰዎች መካከል 228 ሰዎች የሞቱ 26 ሰዎች የተረፉ ሲሆን የቦይንግ ኩባንያ የ747 ምርቶችን ለ20 ቀን አቁሞ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም