የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ስኳር ማምረት ካቆመ ግማሽ ዓመት አስቆጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ስኳር ማምረት ካቆመ ግማሽ ዓመት አስቆጥሯል
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 18/2011 በአፋር ክልል የሚገኘውና ዘመናዊና ግዙፉ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ስራ በአገዳ ግብዓት እጦትና ሌሎች ችግሮች ስራ ካቆመ ግማሽ ዓመት ማስቆጠሩ ታወቀ። ፋብሪካው ስራ ካቆመ ስድስት ወራትን ቢያስቆጥርም ከ14 ሺህ ለማያንሱ ሰራተኞች ለደመወዝ ብቻ በየወሩ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ እየከፈለ መሆኑ ተነግሯል። በአፋር ክልል አሳይታ ወረዳ የሚገኘው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ2007 ዓ.ም ወርኃ ጥቅምት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ተጠናቆ የሙከራ ምርት መጀመሩ ከተነገረለት አራት ዓመታት አስቆጥሯል። የመጀመሪያ ምዕራፍ ፋብሪካው ወደሙሉ አቅሙ ሲገባ በየቀኑ 13 ሺህ ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ያመርታል ቢባልም የሙከራ ምርት ማምረቱ ከተነገረበት ዓመት ጀምሮ በታቀደው መጠን አላመረተም። ባለፈው ዓመት 80 ሺህ ቶን ያመረተው ፋብሪካው በተጠናቀቀው የ2011 በጀት ዓመት 49 ሺህ ቶን ስኳር ብቻ ማምረቱ ተጠቁሟል። የኢዜአ ዘጋቢ ፋብሪካው በሚገኝበት ስፍራ በአካል ተገኝቶ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የፋብሪካው የስራ ኃላፊዎች እንዳስረዱት ፋብሪካው ስራ ካቆመ ስድስት ወራት አስቆጥሯል። ለስራ ማቆሙ ምክንያት ደግሞ የባጋስ ወይም ከስኳር አገዳ ገለባ የሚመነጭ ሃይል እጥረትና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩበትም ለስራ ማቆሙ ቁልፉ መንስኤ ግን በአግሮኢኮሎጂ፣ በድርቅና የሸንኮራ አገዳ ማሳዎች በእንስሳት መጠቃት ሳቢያ የአገዳ እጥረት መከሰቱ ነው። በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ወጭ የተደረገበት የተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በተለይም በድርቅ ወቅቶች በአገዳ ልማቱ ላይ በሚከሰት የእንስሳት ጥቃት አገዳ ማልማት ባለመቻሉ ስኳር ማምረቱን አቁሟል። ፋብሪካው ወደፊትም ወደምርት ለመግባት የግድ የአገዳ ግብዓት ማግኘት የሚያስፈልገው ሲሆን ለዚህ ደግሞ አገዳ ተክሎ ለምርት ለማድረስ ቢያንስ አንድ ዓመት ይፈጅበታል ተብሏል። በዚህም ቢያንስ ለቀጣይ አንድ ዓመትም ወደ ስኳር ምርት ሊመለስ እንደማይችል ተመልክቷል። በአዋሽ ወንዝ ላይ በተሰራው ተንዳሆ ግድብ የሚያለማው የአገዳ ማሳ በተለይም በድርቅ ወራት አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ወደአገዳ ማሳው ሰለሚያሰማሩ የሚተከለው አገዳ ለምርት ማድረስ አለመቻሉን ተጠቁሟል። የአፋር ክልል የኢንቨስትመነት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አሲያ ከማል የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከምስረታው ጀምሮ ለውሃ ግድብና ለሸንኮራ አገዳ ልማት ከአካባቢው ማህበረሰብ መሬት ሲወሰድ ቃል የተገባው የመኖ ልማት አለመዘጋጀቱን ይናገራሉ። የአካባቢው ህብረተሰብም ከፋብሪካው ተጠቃሚ እንዳልሆነና ከፋብሪካው የሚወጣው ሞላለሰስ ተብሎ የሚጠራው ዝቃጭ በእንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰብን ነው በሚል ቅሬታ እንደሚያነሳም ገልጸዋል። ፋብሪካው ሲሰራ ማኅበረሰብ ማማከርና ይሁንታ ማግኘት፣ በተወሰደበት የግጦሽ መሬት ምትክ መፍትሄ ማበጀት ያስፈልግ እንደነበር ገልጸው፤ አሁንም ፋብሪካው ለማስቀጠል ከማህበረሰቡ ጋር በውይይት መፍታት እንደሚቻል ያምናሉ። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጠን ጥረት አድርገን ነበር። የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉህም በተለይም በፋብሪካው አገዳ ልማት ተግዳሮት በተመለከተ በአካባቢው አርብቶ አደሮች ጋር ስለተፈጠረው አለመግባባት በተመለከተ 'ከአቅማችን በላይ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። 'በጉዳዩ ላይ የሚመለከተውን አካል መረጃ እንዲሰጥ አመቻቻለሁ' ብለው ቃል ቢገቡም በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልና ለሳምንታት ብንጠብቅም የተባለውን መረጃ ማግኘት አልቻልንም።