የሃይማኖት ተቋማቱ በ"አረንጓዴ አሻራ ቀን" በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማቱ በ"አረንጓዴ አሻራ ቀን" በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀዋል
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 18/2011 በመጪው ሳምንት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓም በመላው ኢትዮጵያ 200 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ለሚካሄደው የ"አረንጓዴ አሻራ ቀን" መረሐ ግብር አስፈላጊውን የቅድም ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የእምነት ተቋማት አስታወቁ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የኃይማኖት ተቋማቱ አመራር አካላት እንዳሉት አካባቢን ለሰው ልጅ የተመቸ መኖሪያ ማድረግ መለኮታዊ ትእዛዝ ሆኖ ከፈጣሪ የወረደ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው። ይህንን እውን ለማድረግ ከሚያስችሉ ቁልፍ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ደግሞ የደን ኃብትን ማልማትና መጠበቅ በመሆኑ መላው ህዝብ በነቂስ ወጥተው በእለቱ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጥሪ አቅርበዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ሊቀጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ እንደተናገሩት፤ ቤተክርስቲያን የሀገሪቱ የእጽዋት ብዝሃ ሕይወት ሀብት እንዲጠበቅ የበኩሏን ስታደርግ ቆይታለች። አሁንም መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተመናመነ የመጣውን የደን ሀብት ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ምእመኑን ከማስተማር ጀምሮ ተግባራዊ ሥራዎችንም በማከናወን ላይ መሆኗን ገልፀዋል። በዚህ ረገድ በመጪው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መረሐ ግብር ላይ ለመሳተፍም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። በዚህ ቀንም በየሀገረ ስብከቱ በሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማትና አድባራት የችግኝ ተከላ መረሐ ግብር የሚከናወንባቸው ቦታዎች መለየታቸውን ጠቁመዋል። ምእመናንና አገልጋዮች በእለቱ በነቂስ ወጥተው የመረሐ ግብሩ ተሳታፊ እንዲሆኑም ዶክተር አቡነ አረጋዊ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ከፍተኛ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አባልና የታላቁ አንዋር መስጊድ ኢማም ሼህ ጧሀ መሐመድ ሀሩን በበኩላቸው እንደተናገሩት ተፈጥሮን መንከባከብና መጠበቅ ከሃይማኖቱ ትዕዛዛት መካከል አንዱ ነው። "የሰው ልጅ ሲፈጥር ፍጥረታቱን ጭምር እንዲጠብቅ ፈጣሪ ወክሎታል፤ ተፈጥሮን መጠበቅ እራስን መጠበቅ ነው" ሲሉም ሸህ ጧሀ ገልፀዋል። በመሆኑም መንግሥት በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከልና ሀገሪቱን አረንጓዴ ለማልበስ የጀመረው ተግባር በእምነቱ የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰው ምክር ቤቱም ምእመኑን በማስተባበር በተከላ መርሃ ግብሩ በትጋት ለመሳተፍ እየሰራ ነው ብለዋል። ከወዲሁም የታለቁ አንዋር መስጊድ ክፍት ቦታዎችን በችግኝ የመሸፈን ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል። የ"አረንጓዴ አሻራ ቀን" መርሃ ግብርን ለማሳካት የችግኝ መትከያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን፣ በመርሃ ግብሩም ሕዝበ ሙስሊሙ እንዲሳተፍ የቅድም ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁንና ትምህርትም በስፋት እየተሰጠ መሆኑን ሸህ ጧሀ አስረድተዋል። "ፈጣሪ የሰው ልጅን ሲፈጥር በመጀመሪያ የሰጠው ትዕዛዝ ተፈጥሮን እንዲጠብቅ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዘዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ ናቸው። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በደን ሀብቷ ትልቅ ሥፍራ ነበራት ያሉት ፕሬዘዳንቱ፤ አሁን ግን ሰዎች በፈጣሪ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ባለመጠበቃቸውና ባለመታዘዛቸው አብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተራቆቱ እና የአየር ንብረቷም እየተዛባ ነው ብለዋል። በመሆኑም ይህንን ችግር መለወጥ ይቻል ዘንድ በመንግስት በተቀረፀም የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ለመሳተፍ ቤተክርስቲያኒቱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቋን አስረድተዋል። በመጪው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀንም ቤተክርስቲያኗ አጥቢያዎች በሙሉ ችግኝ ለመትከል መረሐ ግብር ወጥቷል ሲሉም ፓስተር ፃዲቁ ገልፀዋል። የሃይማኖት አባቶቹ ችግኝን መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፤ ሁሉም ዜጋ የተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ ለፍሬ እንዲያበቃ አሳስበዋል። በኢትዮጵያ በተያዘው የክረምት ወቅት ከአራት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ነው። ሊተከል ከታቀደው ከዚህ ችግኝ ውስጥም እስካሁን 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን መተከሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል። በመጪው ሳምንት እለተ ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓም ደግሞ በአንድ ጀምበር ከ200 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል ታሪክ ለማስመዝገብ መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል። እስካሁን ህንድ 66 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ቀን በመትከል ክብረ ወሰን የያዘች አገር ናት።