ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የፕሮጀክት ንድፈ ሐሳብ ዝግጅት ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 18/2011 የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የመጀመሪያ ዙር የፕሮጀክት ንድፈ ሐሳብ ዝግጅት ጥሪ አቀረበ። ትረስት ፈንዱ ዛሬ ይፋ ባደረገው የፕሮጀክት ንድፈ ሐሳብ ጥሪ እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል። በተዘጋጀው የፕሮጀክት መመሪያ መሰረት የልማት ስራዎች ፕሮጀክቶችን ሐሳብ በመያዝ ሁሉም ወገን ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል። 'የኢትዮጵያዊያንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሻሻል የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች አጋርነት' በሚል መሪ ሐሳብ ነው የፕሮጀክት ሐሳቡ ይፋ የሆነው። በ77 አገሮች የሚገኙ 24 ሺህ 100 ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች 'በቀን አንድ ዶላር ለተሻለች ኢትዮጵያ' የሚለውን ጥሪ ተከትሎ በተቋቋመው የዲይስፖራ ትረስት ፈንድ በኩል ያደረጉት ድጋፍ አራት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። ይህንን ገንዘብ በኢትዮጵያ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ፕሮጀክቶች ላይ ለማዋል ትረስት ፈንዱ መዘጋጀቱን አስታውቋል። ህጋዊ አካል የሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የግል ዘርፍ ኩባንያዎች የመንግስት ተቋማት እስከ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የፕሮጀክት ሃሳባቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ተገልጿል። ገንዘብ በማዋጣት ከፍተኛ ተሳትፎ ላደረጉ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ምስጋና ያቀረበው ትረስት ፈንዱ፤ በበጎ ፈቃደኝነት ከትረስት ፈንዱ ምስረታ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል። የበጎ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ያላቸውን ሁሉ በመስጠት ላበረከቱት አስተዋጽኦም አመስግኗል። በመላው ዓለም የሚገኙ 39 የዓለም አቀፍ ምዕራፎች የሁሉንም ተሳትፎ ለማረጋገጥ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ሆነው እየሰሩ እንደሆነም ጠቁሟል። የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (ዩኤንዲፒ) የዲያስፖራ ትረስት ፈንዱ ሲቋቋም ጀምሮ እያበረከተ ላለው ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቦ በትረስት ፈንዱ ዓላማዎች አምኖ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል። ለዲያስፖራ ትረስት ፈንዱ አማካሪ ምክር ቤት አባላት ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጾ፤ ለኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ጥሪ በማድረግ ትረስት ፈንዱ እውን እንዲሆን ሃሳብ ላመነጩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያለውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጿል። ‘’ጥሩ መሪዎች ራዕያቸውን ለሌላው አጋርተው በማነሳሳት ራዕያቸው እውን እንዲሆን ያደርጋሉ’’ ብሏል የትረስት ፈንዱ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም