ከክልልነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በንፁሀን ዜጎች ላይ ህገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ለህግ ይቅረቡ- ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከክልልነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በንፁሀን ዜጎች ላይ ህገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ለህግ ይቅረቡ- ፓርቲዎች
ሐምሌ 18/2011 በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከክልልነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በንፁሀን ዜጎች ላይ ህገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ሰባቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳሰቡ። ፓሪቲዎቹ የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ እንደገለጹት በደቡብ ክልል ከክልልነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ ፣ዝርፊያና ወከባ የፈጸሙ ቡድኖች ለህግ መቅርብ ይኖርባቸዋል። ይህም ህዝቡ ለሚያነሳው ጥያቄ አፋጣኝ መልስ ለመስጠትና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል። ፓርቲዎቹ በአሁኑ ወቅት የአገሪቷንና የህዝቦችን አንድነት እያናጋ ያለው የፌዴራሊዝም ስርዓቱን በትክክል ያለመተግበር መሆኑን እንደሚያምኑ ጠቅሰው ከአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ህገ-መንግስቱ ላይ የማሻሻያ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል ሲሉም ገልጸዋል። በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ህይወታቸው ያለፈው ከፍተኛ የመንግሰት ባለስልጣናት ጉዳይ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግና በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች አስቸኳይ ማጣሪያ ተደርጎባቸው ንጹሀን ዜጎች እንዲፈቱም ጠይቀዋል። ፓርቲዎቹ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከተማ መሆኗን ተናግረው የከተማውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ህግን መሰረት ባደረገ ሁኔታ እንዲስተናገድ ሲሉም አክለዋል። መግለጫውን የሰጡት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት (ኢዴህ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ (ኦነንፓ)፣ የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ (አሕነፓ) እና የአፋር ሕዝብ ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አሕፍዴፓ) ናቸው።