ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጂቡቲ አቻው ጋር ነገ ይጫወታል

አዲስ አበባ ኢዜአ ሐምሌ 18/2011 በካሜሮን አስተናጋጅነት በ2020 በሚካሄደው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውን ከጂቡቲ አቻው ጋር ነገ ያካሂዳል። በአገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋጨቾች የሚካፈሉበት የቻን ውድድር በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) በዚህ የቻን ውድድር የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ከጂቡቲ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል ። በአሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ዋልያዎቹ ለዚህ ጨዋታ ቅድመ ዝግጅት ከሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ  በአዳማ ከተማ ልምምዳቸውን ሲያደረጉ ቆይተዋል። ቡድኑ ከትናንት በስቲያ ወደ ጂቡቲ ያቀና ሲሆን በነገው እለት የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ያከናወናሉ። በትናትናው እለትም የመጀመሪያ ልምምዳቸውን በጂቡቲ ሀሰን ጉሌት ኦብቲዶ ስታዲየም ሰርተዋል። በልምምድ ወቅትም የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው አቤል ያለው በጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ምክንያት  ልምምዱን አቋርጦ መውጣቱን ነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያስታወቀው። ካሜሩን የምታስተናግደው የ2020 የቻን ውድድርን ኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ሞሮኮ ላይ በተዘጋጀው ስነ-ሥርዓት ላይ በመገኘት ርክክቡን ፈጽማ የነበረ ቢሆንም የዝግጅት ስራዎች ባለመጠናቀቃቸው ዕድሉ ወደካሜሩን ሄዷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም